በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ግቦችን ለማሳካት የህዝብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ግቦችን ለማሳካት የህዝብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል
አርባ ምንጭ፤መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለማከናወን የተያዙ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ህዝቡ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በአርባ ምንጭ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ለሀገረ መንግስት ግንባታ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ጥበብና ፍልስፍናን ማዕከል በማድረግ እየተሰራ ነው።
የጋሞዎች የሰላም እሴትም ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፣ እሴቶቹን በማጎልበት ልንጠቀማቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና የጎደሉትን ለመሙላት የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በጋሞ ዞን ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ አርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ግቦች እንዲሳኩ የመንግስትና የህዝብን አቅም በማስተባበር ይሰራል ብለዋል።
በመደመር መንግስት የዲጂታል ሥርአትን በማጎልበት ከዓለም ጋር ዕኩል ለመጓዝ ያለእረፈት ይሰራል ብለዋል።
በተለይ ህዝቡ ሰላምና አንድነቱን በመጠበቅ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡