የትምህርት ጥራት - የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ችቦ የትውልድ ብሩህ ፋና - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራት - የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ችቦ የትውልድ ብሩህ ፋና
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት፤ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የትምህርት ጥራት የበለጠ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ስልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር አበክረን እንሰራለን፤ ህብረተሰቡ በሞራል፣ በእሴት፣ በክህሎት እንዲሁም በሀገራት ስሜት የሚታነጽበት መንገድ እንከተላለን ብለዋል።
የትምህርት ሥርዓት የትኛውም ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀረጽበት፣ የሥልጣኔ ቀጣይነት የሚረጋገጥበትና የትውልድ አቅም የሚገነባበት ታላቁ የሀገር ግንባታ መሣሪያ ነው። መንግሥትና ሕዝብ ተባብረው መንገድና ድልድይ ሊገነቡ፣ ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎችን ሊገነቡ ወይንም ግዙፍ ፋብሪካዎችን ሊያቆሙ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ መሠረተ ልማቶች ቀጣይነት ሊኖራቸው የሚችለውና ፍሬ የሚያፈሩት የሚንከባከባቸው፣ የሚያሻሽላቸውና አዲስ ዕውቀት የሚያመነጭ ብቁና ንቁ ትውልድ ሲኖር ብቻ ነው። በመሆኑም የመደመር መንግሥት በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገው ኢንቨስትመንት በሀገር የወደፊት ጽኑ ሕልውናና ዘላቂ አቅም ላይ የሚደረግ ታላቅ መዋዕለ ነዋይ ነው።
ይህ የተቀናጀ የለውጥ አጀንዳ ከአንድ ነጠላ ፕሮጀክት ወይም ከአንድ የትምህርት ደረጃ ብቻ የሚጀምር ሳይሆን፣ ከተማሪው ዕለታዊ ሕይወት እስከ ሀገራዊ የዕውቀት አቅም ድረስ የተዘረጋ ሰፊ ርዕይ ነው፡
👉የተማሪዎች ምገባ (የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲ)፡-
በረሃብ የሚሰቃይ ተማሪ በትምህርቱ ላይ ትኩረት ሊያደርግ አይችልም። ረሃብ የመማር ፍላጎትን ከመቀነሱም በላይ ልጆችን ከትምህርት ገበታ ያርቃል። ይህንን እውነታ በመረዳት መንግሥት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንደ አንድ ትልቅ የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲ ተወስዷል። ይህም ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲቀጥሉ ከማድረጉ ባሻገር፣ ሁሉም በአንድ ማዕድ እኩል ተቀምጠው እንዲመገቡ በማድረግ በልጆች ዘንድ የእኩልነት፣ የአብሮነትና የማኅበራዊ መተሳሰብ ስሜትን አጎልብቷል።
👉የመምህራን ብቃትና ሙያዊ ማሻሻያ፡-
ጥራት ያለው ትምህርት በብቁ መምህራን ይረጋገጣል። መንግሥት መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ጎን ለጎን በመምህራን ሙያዊ ብቃትና ዘመናዊ የማስተማር ክህሎት ላይ አድርጓል። መምህራን እውቀት አጋሪ፣ መሪና አዳዲስ እሳቤዎችን የሚቀርጹ የትውልድ ሞዴል እንዲሆኑ በማስቻል፣ የትምህርት ጥራት ትርጉም ባለው መልኩ ወደ ተማሪዎች እንዲሸጋገር ተደርጓል።
👉መሠረተ ልማትና የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፡-
ቁጥርን ከጥራት ጋር ያገናኙ በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ደረጃቸውን ያሻሻሉ ተቋማት ተገንብተዋል። በተለይም የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች አፈላልጎ በመቀበል፣ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ የታገዘ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
👉የንባብ ባህልና የቴክኖሎጂ ምጥቀት፡-
ትምህርት በክፍል ውስጥ ብቻ የሚገደብ ባለመሆኑ፣ እንደ አብርሆት ያሉ ታላላቅ ቤተ-መጻሕፍት ተገንብተዋል። ይህም በንባብ የሚገነባ፣ ጥያቄ የሚጠይቅና የሀገርን የዕድገት አቅጣጫ በአዎንታዊ መልኩ መቀየር የሚችል ትውልድ ይፈጥራል። በተጨማሪም፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂንና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ሥልጠናዎችን በማስፋፋት ተማሪዎች የዓለምን የቴክኖሎጂ ምጥቀት እንዲቀስሙና አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያመነጩ መንገድ ተከፍቷል።
👉ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የምርምር ማዕከል ማድረግ፡-
ዩኒቨርሲቲዎችን ከዲግሪ ማደያነት አውጥቶ በዘመናዊ ቤተ-ሙከራዎችና የምርምር አቅም በማጠናከር የሀገሪቱን ችግሮች በሳይንሳዊ መንገድ የሚፈቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የማዕከል ቦታዎች እንዲሆኑ ተደርጓል።
በዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተልዕኮ የመለየት ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን የምርምር፣ የተግባር ሳይንስ ፣ አጠቃላይ ወይንም ሁለንተናዊ እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ ዩኒቨርሲቲዎች በሚል ተከፋፍለው ትውልድን በማብቃት ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ መልኩም ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም ተቋማቱ በራሳቸው አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ነፃነት በመመራት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ፣ የላቀ የምርምር አቅም እንዲገነቡና ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።