በመልካ አቴቴ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ባህልና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በመልካ አቴቴ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ባህልና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል
ሸገር ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ መልካ አቴቴ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ባህልና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።
በሸገር ከተማ በቡራዩ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የመልካ አቴቴ ስፍራ “ኢሬቻ ለብሔራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል በማስመልከት ከወጣቶችና ሴቶች ጋር ዛሬ ውይይት ተደርጓል።
የቡራዩ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ አባታ አስራት በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዓሉን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል።
የመልካ አቴቴ ኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ማንነትና ባህል ማሳያ ከሆኑት እሴቶች አንዱ መሆኑን ያነሱት አቶ አባታ፣ በዓሉ የሰላምና የአንድነት ምልክት መሆኑንም ገልጸዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የአንድነትና የማኅበራዊ መግባባት መገለጫ በመሆኑ ባህላዊ ሥርዓቱንና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ከአባ ገዳዎች፣ ከወጣቶችና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት በዓሉ የሚከበርበትን አካባቢ የማጽዳት፣ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ የማድረግ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የማስፋፋትና የማስዋብ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በተለይ የከተማው ወጣቶች ከጎቤና ሺኖዬ በዓላት ጀምሮ እስከ ኢሬቻ መልካ አቴቴ በዓል ድረስ በተለያዩ ተግባራት መሳተፋቸውን ጠቁመው፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ለበዓሉ የሚታደሙ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጨምሮ ሌሎች እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የጸጥታ አካላት በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቶችም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የክፍለ ከተማው የወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ሲሳይ ሞአ በበኩሉ፤ ወጣቶችን በማደራጀት ለበዓሉ ለሚመጡ እንግዶች አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።
በተለይም ወጣቱ ከጸጥታ አካላትና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት በዓሉ በድምቀት እንዲከበር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፈችው ወጣት አዲሴ በቀለ በበኩሏ፤ በዓሉ ባህሉንና እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመደራጀት የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ተናግራለች።
የእሬቻ መልካ አቴቴ በዓል ሰላምን፣ አንድነትንና ማህበራዊ መግባባትን በማጠናከር እንዲሁም የኦሮሞን ባህልና ማንነት ለተከታታይ ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።
የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የእሬቻ በዓል ባሳለፍነው መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም በድምቀት መከበሩ ይታወሳል።