ቀጥታ፡

በከተማው የመስኖ ልማቱን በማዘመን ለገበያ የሚሆን ምርት ለማምረት ትኩረት ተደርጓል

ደብረ ብርሃን  ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሃን ከተማ የመስኖ ልማቱን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት ለማምረት ትኩረት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ። 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የበጋ መስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሄዷል።


 

በወቅቱም ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ እንደገለጹት፤ የመስኖ ልማቱን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት ለማምረት በትኩረት ይሠራል።

በዘርፉ የሚሰማሩ አርሶ አደሮች ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በማምረት በከተማዋ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን መጠቀም፣ ግብዓትን በአግባቡና በወቅቱ ማቅረብ እንዲሁም አዳዲስ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎችን መተግበር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የበጋ መስኖ ልማትን ከከተማ ግብርና ጋር አስተሳስሮ በማልማት የምርታማነት እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መርሻ አይሳነው በበኩላቸው፤ የግብርናውን ዘርፍ ከምርታማነት ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በያዝነው በጋ በከተማ አስተዳደሩ 6 ሺህ 661 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው፣ ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ ሄክታሩ አዲስ የተካተተ መሬት መሆኑን ተናግረዋል።

ከአጠቃላይ መሬቱ ውስጥ 5 ሺህ 680 ሄክታር የሚሆነው በበጋ ስንዴ የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም 882 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችና 23 የእርሻ ትራክተሮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ገልጸዋል።


 

ከጽጌሬዳ ቀበሌ የመጡት አርሶ አደር ቄስ ታደሰ በቀለ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት አንድ ሄክታር ማሳቸውን በኩታ ገጠም በስንዴ በማልማት 39 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በያዝነው በጋም ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በስንዴ በመሸፈን ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት አቅደው ሥራ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ከጨፈና ቀበሌ አርሶ አደር አድማሱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በተያዘው የበጋ ወራት አንድ ሄክታር መሬታቸውን በበጋ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም