ቀጥታ፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሳደገ ነው

ነቀምቴ፤ መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፡- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከምርምር ማዕከላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሳደገ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ሥርፀት ኦፊሰር ተመራማሪ ጋዲሳ ተሾመ ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ከባኮ ብሔራዊ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር BH-520 የተሰኘ የተሻሻለ የበቆሎ ዝርያን በማባዛት የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሳደገ ነው።

ይህም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እያጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለ300 የአርሶ አደር ማሰራጨቱንም ተመራማሪው ገልጸዋል።

የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት የሚያግዙ የአትክልት ዘር ማቅረብና ተጠቃሚዎችም ውጤታማ እንዲሆኑ ሙያዊ ድጋፍ  ማድረጉን አንስተዋል።

በቀጣይም የግብርናን ውጤታማነት በማሳደግ አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን የሥልጠናና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።

ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ለአርሶ አደሩ የሚያቀርቡት የግብርና ቴክኖሎጂ የአርሶ አደሮችን ምርታማነትን ማሳደጉን የገለጹት ደግሞ የዋዩ ቱቃ ወረዳ ግብርና ባለሙያ አቶ ሚልኬሳ ነመራ ናቸው።

ይህም የአርሶ አደሩን የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችንና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ባህል እያዳበረው መምጣቱን ገልጸዋል። 

ዩኒቨርሲቲው የሚያቀርበው የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ከአካባቢው የአየርና የአፈር ሁኔታ ጋር የሚስማሙ መሆናቸው   ለምርታማነት ማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።

የዋዩ ቱቃ ወረ ባቦ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ መልካሙ ሀነቢሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ከዩኒቨርሲቲው ያገኙትን የተሻሻለ የበቆሎ ዘር ተጠቅመው ምርታማነታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የቤተሰባቸውን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዳገዛቸው ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያቀረበላቸው የተሻሻለ የሰብል ዝርያና የግብርና ቴክኖሎጂ ድጋፍ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንዳገዛቸው  የጠቆሙት ደግሞ ሌላው ተጠቃሚ አርሶ አደር ጀቤሳ ቱፍ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ውጤታማ እንዲሆኑ ያበረከተላቸው አስተዋጽኦ በኑሮዋቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣቱ  ተሞክሯቸውን  ለሌሎች አርሶ አደሮች እያካፈሉ መሆናቸውን  ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም