ገቢር-ነበብ ዲፕሎማሲ፤ የመደመር መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ መርህ - ኢዜአ አማርኛ
ገቢር-ነበብ ዲፕሎማሲ፤ የመደመር መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ መርህ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ ፣ ታላቅ ርዕይ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ አንድ ጉልህ ለውጥ- ዲፕሎማሲው ከምላሽ ሰጪ አቀራረብ ወደ ገቢር ነበብነት፣ ተሳታፊና ሀገራዊ ጥቅምን በግልጽ ወደሚያስቀምጥ አቅጣጫ ተሸጋግሯል።
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት አቀራረብ የሀገሪቱን ጥቅም ከጎረቤት ሀገራት ጥቅም፣ ከቀጣናዊ ሰላም፣ ከአህጉራዊ ትብብርና ከዓለም አቀፍ አጋርነት ጋር በማስተሳሰር የሚጓዝ ነው። ይህም ሀገራዊ ጥቅምን መተው ሳይሆን፣ የራስን ጥቅም ከሌሎች ጋር በሚያጣጥም መንገድ ማሳካትን የሚያስችል የጋራ ተጠቃሚነት አስተሳሰብ ነው።
👉ቅድሚያ ለጎረቤት፤ የጋራ ጥቅም የዲፕሎማሲው መሠረት
የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ግንኙነት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በቀዳሚነት ማስቀመጡ የዲፕሎማሲው አንዱ ጉልህ መገለጫ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ያለው የሰላምና ደህንነት ሁኔታ፣ የንግድ ትስስር፣ የህዝብ እንቅስቃሴ፣ የውሃና የኃይል ሀብት፣ የመሠረተ ልማት ትስስርና የባህር መዳረሻ ጉዳዮች በአንድ ሀገር ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም።
ስለዚህም ነው የመደመር መንግሥት የጎረቤት ፖሊሲ ሀገራዊ ጥቅምን ከቀጠናዊ ጥቅም ጋር በማጣመር እያስኬደው የሚገኘው። ይህም የጎረቤት ሀገር መረጋጋት ለኢትዮጵያ መረጋጋት፣ የጎረቤት ኢኮኖሚ መጠናከርም ለኢትዮጵያ ንግድና ኢኮኖሚ እድል ነው ከሚለው አስተሳሰብ ይነሳል።
ይህንኑ አቅጣጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን መጀመሪያ መደበኛ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ብሔራዊ ጥቅሟን መሠረት አድርጋ እንደምትሰራ ነው የገለጹት። በዚህም ጎረቤት ሀገራት በተፈጥሮ የተገናኙ ወዳጆች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅምና በትብብር የመስራት መርህን እንደሚያስቀጥሉ ነው የገለጹት።
👉የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ፤ ሀገራዊ ጥቅም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ የሀገሪቷ የውጭ ፖሊሲ ከሚያተኩርባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ ከዓለም ገበያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማስፋትና የሎጂስቲክስ ወጪዎችን ለመቀነስ የባህር መዳረሻ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ጥቅም በማድረግ በትኩረት እየሰራችበት ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት የመደመር መንግስት የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን እንደማይችል እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሀገሪቷ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት እየሰራ ይገኛል። ይህም ጉዳዩን ከጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነትና ከቀጣናዊ ሰላም ጋር በማጣጣም በድርድርና በጋራ ጥቅም መርህ መፍትሔ ለመፈለግ ያለውን አቅጣጫ ያሳያል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቁመና በሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ የሚወሰን አይደለም። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ በአህጉራዊ የፖለቲካ፣ የሰላም፣ የደህንነትና የልማት አጀንዳዎች ላይ ለኢትዮጵያ ልዩ የዲፕሎማሲ ቦታ ይሰጣታል። በአፍሪካ ህብረት ያላት ተሳትፎም አህጉራዊ ትብብርን ከሀገራዊ ጥቅም ጋር ለማጣመር የሚያስችል መድረክ ነው። ይህም የመደመር እሳቤን ከሀገራዊ ድንበር አልፎ አፍሪካዊ ትብብርን እንደ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መሠረት የሚመለከት መሆኑን ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከጃንዩወሪ 1 ቀን 2024 ጀምሮ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ በውጭ ግንኙነቷ የተጨመረ አዲስ የዲፕሎማሲ መድረክ ነው። አባልነቱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከገልፍና ከሌሎች የግሎባል ሳውዝ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከርና የዲፕሎማሲ አማራጮቿን ለማስፋት ዕድል ፈጥሯል።
ብሪክስ ከኢኮኖሚና ከፋይናንስ ትብብር ባሻገር በዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ፣ በደቡብ ደቡብ ትስስር ድምፅ መጠናከርና በብዙ ወገን ትብብር ዙሪያ የሚካሄዱ ውይይቶች መድረክ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ አማራጭ ይፈጥራል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከጎረቤትና ከአፍሪካ ደረጃ ባሻገር ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከሩሲያ፣ ከቱርክ፣ ከገልፍ ሀገራት፣ ከአውሮፓና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እያሰፋች ትገኛለች። ግንኙነቱም በፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ሳይወሰን ኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኃይል፣ መሠረተ ልማትና የሰው ኃይል ልማትን ያካትታል።
ይህ አቀራረብ ዲፕሎማሲው የውጭ ፖሊሲ ግቦችን ብቻ ሳይሆን የልማት ፍላጎቶችንም የሚያገለግል መሣሪያ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። በዚህም የዲፕሎማሲ ስኬት በተፈረሙ ስምምነቶች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በሚፈጠሩ የኢኮኖሚ እድሎች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልማት ትብብር የሚመዘን ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ሀገሪቱ የውጭ ግንኙነቷን ከሀገራዊ ጥቅም ጋር አጥብቃ በማስተሳሰር የዲፕሎማሲ አማራጮቿን እያሰፋች መምጣቷን ያሳያል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ጥቅምን መሠረት ማድረግ፣ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይን በድርድር ለመፍታት መስመር መክፈት፣ በአፍሪካ ህብረት ተሳትፎን ማጠናከር፣ በብሪክስ መሳተፍና ከተለያዩ የዓለም ኃይሎች ጋር ግንኙነትን ማስፋት የዚህ አቅጣጫ ዋና መገለጫዎች ናቸው።
የዛሬው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቁመና ከጎረቤት ግንኙነት ወደ ቀጣናዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ትብብር፣ ከአህጉራዊ ተሳትፎ ወደ ዓለም አቀፍ የባለ ብዙ ወገን መድረኮች የሚዘልቅ ሰፊ አውታር እየገነባች መምጣቷ እውን ነው።
የዚህ ጉዞ ዋና ገፅታም ሀገራዊ ጥቅምን በግልጽ ማስቀመጥ፣ የጎረቤቶችን ጥቅምና ሉዓላዊነት ማክበር፣ የቀጣናውን ሰላም ከሀገራዊ ጥቅም ጋር ማስተሳሰርና በተለያዩ የዓለም ዲፕሎማሲ መድረኮች ተሳትፎን ማስፋት ነው። በዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቁመና በገቢር ነበብ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም እያስቀመጠች ከጎረቤት፣ ከአህጉርና ከዓለም ጋር የጋራ ጥቅም የሚፈጥር የዲፕሎማሲ መስመር እየገነባች መሆኗን የሚያሳይ አቅጣጫ ሆኗል።