ቀጥታ፡

ማዕከሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል

ጅማ፣መስከረም 28/2019(ኢዜአ):- የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የቡና ምርትን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ።

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ለሚ ቤክሲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የምርምር ማዕከሉ በጅማ አካባቢና ለቡና ልማት ምቹ በሆኑ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች  በሽታን የሚቋቋሙና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በተለያዩ ተቋማት በኩል ለአርሶ አደሩ እያደረሰ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በአርሶ አደር ማሳዎች እና የሰርቶ ማሳያዎችን በማቋቋም የቡና ቴክኖሎጂዎች እንዲተዋወቁ እያደረገ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ 51 የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 9ኙ ዲቃላ የቡና ዝርያዎች ሲሆኑ፣ በሄክታር ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ማዕከሉ በየዓመቱ ከ200 ኩንታል በላይ የቡና ምርጥ ዘር እንዲሁም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ ሲያሰራጭ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የቡና ጥራትን ለማስጠበቅም ባለሙያዎችን በማሰማራት በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ለሚ አክለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ሰቃ ጮቆርሳ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር  ዛኪር አባዝናብ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል በማዕከሉ በኩል የቀረበላቸውን የተሻሻለ የቡና ዝርያ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ሰፋ ባለ መሬታቸው ላይ በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎች እያለሙ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ማዕከሉ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።

ሌላው የማና ወረዳ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ነጂብ አባዱራ በበኩሉ፣ በግብርና ምርምር ማዕከሉ በኩል የቀረበለትን የተሻሻለ የቡና ዝርያ በማልማት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

የተሻሻለው የቡና ዝርያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ገልጾ ወደፊትም ዝርያውን በስፋት እንደሚያለማ አመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም