ቀጥታ፡

የሀገር ሃብትን መግለጥ - ልማትን ማሳለጥ

የአባይ መነሻ፣ የዓለም የዲፕሎማሲ መናገሻ የሆነችው ታላቋ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህልና ቅርስ ሃብታም ሀገር ነች። ኢትዮጵያ ገና ብዙ ተገልጠው ያላለቁ እምቅ ሃብቶች ያሏት በመሆኑ ሃብቷን የመለየትና የማወቅ፣ የመጠበቅ፣ የማልማትና ለህዝብ ጥቅም የማዋል ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እምቅ የሀገር ሀብቶችን አልምቶ ከመጠቀም ባሻገር የልማት አቅሞችን በመለየት ወደ ኢኮኖሚ ዕድል የመቀየር ሂደትም ቀጥሏል። የሀገርን እምቅ ሃብቶች በመግለጥ በተደመረ አቅም በማልማት ረገድ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት አስደናቂ ተግባራትን ፈፅሞ ውጤትም ማምጣቱ ይታወቃል።

በህዝብ ይሁንታ ሌላ የመምራት እድል የተሰጠው የመደመር መንግሥት የማልማትና ህዝብን ተጠቃሚ የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የታሪክና የሥልጣኔ አሻራዎች፣ የባህልና የሃይማኖት ቅርሶችና ሌሎችም የኢትዮጵያ የቱሪዝም አቅሞች ሆነው የሚቀጥሉ ይሆናል።

ከባሌ ተራሮች እስከ ኤርታሌ፣ ከአዋሽ እስከ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርኮች፣ የጣና ሀይቅን ጨምሮ ሌሎችንም ባክነውና ተደብቀው የቆዩ ሃብቶችን በማልማት ጥቅም ላይ ውለዋል። እነዚህን ሀብቶች ማልማት ማለት ቱሪስቶችን ብቻ መሳብ አይደለም። መንገድን ማሻሻል፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የመስተንግዶ አቅምን ማሳደግ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራና የገቢ ዕድል መፍጠር እና የተፈጥሮና የባህል ሀብቶችን መጠበቅ ጭምር ነው። በመሆኑም የቱሪዝም ልማት ሀገርን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር የሃብት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የሀገርን እምቅ አቅም በመግለጥ ከተሞችና ገጠርን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ህዝቡ እንዲጠቀም እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ሀገርን ይበልጥ ያስተሳስራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያፋጥን ይሆናል።

በመሆኑም የመደመር መንግስት እነዚህን መልካም ጅምሮች አጠናክሮ በመቀጠል የሀገርን ልማት እድገትና ማንሰራራት ማስቀጠል ይጠበቅበታል። የመደመር መንግሥት አቅዶ መሥራት፣ ጀምሮ ማጠናቀቅና ለህዝብ አገልግሎት ማብቃት የሚለውን የሥራ ባህል ይበልጥ ማጠናከርም ይኖርበታል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ያልተገለጡ አቅሞችን የማሳየት፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የማላቅና የማጠናቀቅ ዘመን እንደሚሆንም ይጠበቃል። የሀገሪቱ የልማት ፍላጎት ሰፊ በመሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመር በጥራትና በፍጥነት የማከናወን እንዲሁም ቀደም ሲል የተጀመሩትን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ይገባል። የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ከ“ምን ታቀደ?” ወደ “ምን ተጠናቀቀ?” እና “ለህዝብ ምን ጥቅም አመጣ?” በሚል የውጤት መለኪያ መሰረት መቀጠል አለበት።

ኢትዮጵያ ብዙ ያልተገለጠ ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ አሁን ላይ ሃብት አለን ወይ? የሚለው ሳይሆን፣ ያለንን ሃብት በምን ፍጥነት፣ በምን ጥራትና በምን ዓይነት ልማት የጋራ ጥቅም ላይ እናውለው? የሚለው ነው፤ ለዚህም የመደመር መንግሥት በጠንካራና ቀጣይነት ባለው ልማት ምላሽ መስጠቱን የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም