በከተማው አገልግሎትን በተሻለ ቅርበትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው አገልግሎትን በተሻለ ቅርበትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ይጠናከራል
ጊምቢ ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ በጊምቢ ከተማ አገልግሎትን በተሻለ ቅርበትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ፈዬራ አቦማ ገለጹ።
በከተማው «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዛሬው ዕለት ወደ ሥራ ገብቷል።
ከንቲባ ፈዬራ አቦማ በምረቃው ወቅት እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ሥራ መግባቱ ለማኅበረሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዩ ማኅበረሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ፣ በአጭር ጊዜና በቅርበት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
ይህም በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ጊዜያት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ አሰራሮችን በማስቀረት ማኅበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎትን በማስፋፋት፣ በተሻለ ቅርበትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ፈዬራ አረጋግጠዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የምዕራብ ኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሊላ ተረፋ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለማኅበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ወደ ተግባር የገባው የጊምቢ በ«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለመስጠት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
ይህም የጊምቢ ከተማና የአካባቢው ማኅበረሰብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያስቀር መሆኑን አመልክተዋል።
የጊምቢ «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለከተማዋ ነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።