የመደመር መንግስት ያስቀመጣቸው የልማት ዕቅዶች ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ያስቀመጣቸው የልማት ዕቅዶች ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው
አሶሳ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ያስቀመጣቸው የልማት ዕቅዶች ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
አዲስ የተመሠረተው የመደመር መንግሥት ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የመደመር መንግሥት በአምስት ዓመታት ውስጥ የሚያከናውናቸውን የልማትና ግዙፍ ሀገራዊ ትልሞች ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡና የዜጎችን ሕይወት የሚቀይሩ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የመደመር መንግሥት ያስቀመጣቸው የአምስት ዓመታት የልማት ዕቅዶች ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ መሠረት የሚጥሉ ናቸው ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሸንገል፤ መንግሥት ያቀዳቸው የልማት ሥራዎች አሻጋሪና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተነሱት ሀሳቦች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አብዱሰላም፣ ለዚህም በአሳታፊነት ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የመደመር መንግሥት በሀገሪቱ ሰላም እንዲፀና፣ የልማት ሥራዎች ተደራሽነት እንዲስፋፋና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገር ልማት ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ልምዱ ለሀገር እድገት የራሱ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፣ ፓርቲያቸውም ለዚሁ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለሜሳ ኔኖ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና በሕብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጧቸው የአምስት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬታማነት በሁሉም መስክ ድልን መቀዳጀት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ በሁሉም ዘርፍ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል።