ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው አስችሏል

ሮቤ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በቅልጥፍና እንዲስተናገዱ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር በተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው አስችሏል ሲሉ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኢድሪስ ተናገሩ።

በደሎ መና ከተማ የተገነባው መሶብ የአንድ መዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

አስተዳዳሪው እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግሥት ዜጎች ከመንግሥት የሚያገኙትን መሠረታዊ አገልግሎቶች የማዘመን ሥራ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።


 

በተቋማት የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥና የቅልጥፍና ችግር ለመፍታት «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ መፍትሔ መሆኑንም ተናግረዋል።

«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በክብርና በቅልጥፍና እንዲስተናገዱ እንዲሁም በተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ፍትሐዊና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ከንክኪ የጸዳና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት የተቀላጠፈ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።


 

«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለተያዘው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ አጋዥ እንደሆነ አቶ አሕመድ ጠቁመው አገልግሎቱ ዜጎችን ከአላስፈላጊ ወጪ የሚታደግና እርካታን የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግሥት አዲስ አደረጃጀትን በመዘርጋት መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ለማቅረብ ያካሄደው የሪፎርም ሥራ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አስታውሰዋል። 


 

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዑመር መሐመድ በበኩላቸው፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ 82 አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሁሉም ዜጎች በእኩል የሚስተናገዱበት አካታች ሥርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ቀልጣፋ አገልግሎትን በአንድ ማዕከል ማግኘት ቀደም ሲል ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀርም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም