የመደመር መንግስት ለሕዝብ የገባው ቃል ስኬታማ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ለሕዝብ የገባው ቃል ስኬታማ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን
ባህር ዳር ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግስት በህዝብ ተሳትፎ ስኬታማ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንደግፋለን ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ታደለ ስማቸው ለኢዜአ እንደገለጸው፣ አዲሱ የመደመር መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ያቀዳቸው ተግባራት እንዲሳኩ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን።
በተለይም የሕዝብ ተሳትፎን ለማሳደግና ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተገንዝበናል ነው ያለው።
ከዚሁ ባሻገርም መንግስት በእቅዱ የባሕር በርን ለማስመለስ እየሔደ ያለው ርቀት የሀገር ሕልውናና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር መሆኑን በመገንዘብ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ነው ያለው።
ሀገሪቱ የጀመረቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ዳር እንዲደርሱና እቅዶች እንዲሳኩ ከአዲሱ መንግሥት ጎን እንሰለፋለን ያሉት ደግሞ ወጣት ጌታሁን ደሴ እና ወጣት ብርቱካን ያዜ ናቸው።
በሀገሪቱ የተሻሉ እና ስኬታማ ልማቶችን ተግባራዊ በማድረግ መንግስት ሲከተል የቆየው አቅጣጫ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደገ በመሆኑን በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት የላቀ ተሳትፎ እናደርጋለን ነው ያሉት።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የተመዘገበውን ሁለንተናዊ ድል ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ውስጥም ግንባር ቀደም እንደሚሆኑም አብራርተዋል።
መንግስት ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት የጀመራቸውን ተግባራት በተጠናከረ ሁኔታ በመቀጠል ወጣቱን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባም ተናግረዋል።