ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት የሕዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ውጤታማ ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግስት የሕዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ውጤታማ የልማት ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በመደመር መንግስት እሳቤ በመመራት ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ፤ አንግባ ይህንን ትልቅነቷን አጠናክረው ለሚያስቀጥሉ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት ቀን ከሌት እየተጋች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል። 

ምክር ቤቱ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሰየሙና እርሳቸውም በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ባለፉት ዓመታት በልማት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በዲፕሎማሲና መሰል ተግባራት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በዛሬው ዕለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያቀረቧቸውን አዲስ ሚኒስትሮች ሹመት ተቀብሎ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፣ እነዚህ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ግሩም ከበደ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ መመረጣቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ተግባራት ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አምስት ዓመታት መንግስት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ውጤታማ የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታመነ ነጉ፣ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉት የልማት ሥራዎች ለሀገራዊ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ዕድገት በበለጠ ውጤታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያደርገው ጥረት ህዝቡ ከጎኑ በመሆን ሊደግፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

አቶ ይልማ ሽመልስ እና አቶ ናስር ሽፋ በበኩላቸው፣ መንግስት የጀመራቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የነገውን ትውልድ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው፣ ለውጤታማነታቸው በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የመደመር መንግስት በቀጣይ አምስት ዓመታት ለመተግበር ያቀዳቸው ዕቅዶች በሀገር አጠቃላይ ዕድገት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጡ ጠቁመው፣ ለስኬታቸውም የዜጎች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም