ቀጥታ፡

የወል ትርክት ግንባታ ለጠንካራና ህብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግስት መሰረት

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፡ ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ የሆነው የወል ትርክት ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት መገንባት ወሳኝ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተሳስርና የጋራ እሴቶችን የሚያጎላ የወል ትርክት የመገንባት ሥራ ቀዳሚው እና ዋነኛው መሠረት ነው።

የመደመር መንግሥት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን እውን ለማድረግ እንዲሁም አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የወሰዳቸው እርምጃዎች የወል ትርክትን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ያለሙ ናቸው። ይህም የሕዝቦችን የጋራ ፍላጎት በማቀናጀትና የፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የሰላም ግንባታ ዕድሎችን ለማስፋፋት የላቀ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክሩ የመላው የኢትዮጵያ ዜጎችን ሐሳብና ድምፅ በአንድነት ያሰባሰበ መድረክ በመሆኑ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነትና "የያገባኛል" መንፈስ እንዲጎለብት ማስቻሉን መመልከት ተችሏል። ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት በዚህ ሂደት፣ የጋራ እሴቶችን በማጎልበት ረገድ አዎንታዊ ምዕራፍ ተከፍቷል።

ከዚሁ ጎን ለጎን፣ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የተወሰዱት አዎንታዊ እርምጃዎች የጋራ አስተሳሰብንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጠናክሩ ናቸው። ይህም የኢትዮጵያን የነገ ጉዞ በተስተካከለ መንገድ ለመምራትና የጋራ የወል ትርክትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።

የወል ትርክት ግንባታ በባዶ መሬት ላይ የሚከናወን ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ያበለጸጉዋቸውን አሰባሳቢ እሴቶች መሠረት ያደረገ ነው። የሕዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክሩ የአደባባይ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት፤ እንዲሁም በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ማኅበረሰቡን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የጋራ ኩራትና የነፃነት ምልክት የሆነው የዓድዋ ድል፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት ቆመው ያሸነፉበትና የጋራ ማንነታቸውን ያረጋገጡበት አሰባሳቢ ትርክት ነው። በዘመናዊው ምዕራፍ ደግሞ የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ፣ ሀብትና ዕውቀት የፈሰሰበት ታላቅ የጋራ ስኬት በመሆኑ የወል ትርክት ግንባታ ሌላው ማሳያና መሠረት ሆኖ ያገለግላል። እነዚህ እሴቶችና ስኬቶች የሕብረተሰቡን አብሮነት በማጠናከር ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸውን አዎንታዊ ሚና ማጎልበት ተችሏል።

መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ከኢኮኖሚ ማጠናከር ባለፈ ለወል ትርክት ግንባታ መጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ታስቦ የተቃኘ ነው። የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ እውን መሆን የላቀ ሚና ይጫወታል።

በገንዘብ ፖሊሲዎች ማሻሻያ አማካኝነት የዕዳ ጫናን መቀነስ፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋትና ገቢን ማሳደግ መቻሉ የዜጎችን እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል። በተለይም በግብርናው ዘርፍ በተካሄደው የልማት እመርታ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ አምራችነት ራስን የመቻል ስኬት እና የሰብል ክላስተር እርሻዎች የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የሕዝብን ድህነት የመቀነስና የሀገር አቅምን የማሳደግ ሕልምን እውን አድርገዋል። ዜጎች በልማት ሂደቱ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሲሆኑ ለሀገራዊ እድገት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የወል ትርክትን በተግባር ለማጠናከር አስተማማኝ መንገድ ሆኗል።

በአጠቃላይ የወል ትርክትን ማጎልበትና ማጠናከር ለጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ምሦሶ ነው። አሰባሳቢ ታሪካዊ እሴቶችን ከመፍጠር ባሻገር፣ አካታች የፖለቲካ ምኅዳርን ማስፋፋት፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ማጠናከር እና የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ማስቀጠል የወል ትርክትን እውን የማድረጉ ሂደት አካላት ናቸው። በመሆኑም የወል ትርክት ግንባታን ማጎልበት የሀገርን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ሂደት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም