ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት - የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፡-የመደመር መንግሥት የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

በሀገሪቱ የተካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ መንግሥት መመስረቱ ይታወቃል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርጎ ሰይሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ በቀጣይ አምስት ዓመታት በመንግስት የሚከናወኑ ጉልህ ተግባራትን ማብራራታቸው ይታወሳል።

በዚህ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት አዲሱ የመደመር መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚያከናወናቸው ተግባራት የሚያደርጉትን አስተዋጾ እንደሚያጠናክሩ ጠቅሰዋል።

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ከድር ሰኢድ የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ገንዘብ በማጠናቀቅ ያሳየውን ቁርጠኝነት  በቀጣይም በማጠናከር  የሕብረተሰቡን  ተጠቃሚነት ማሳደግ  እንዳለበት ገልጸዋል።

እንደ ኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሉ ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።


 

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት አሚንመሐመድ መንደል በበኩሉ እንዳለው፣ የመደመር መንግሥት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሄደበት ርቀት የሚበረታታ በመሆኑ ለቀጣይ የያዛቸው ግቦች እንዲሳኩ ዜጎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ጠቅሷል። 

በመተባበር የማናሳካው ልማት እንደሌለ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ጥሩ ማሳያ በመሆኑ አዲሱ መንግስትም የተጀመሩና አዲስ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ልማቱን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። 

መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች በተሳካና በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ በተግባር አሳይቶናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው ነዋሪ አቶ ቦሬ ጦይብ ናቸው።


 

የመደመር መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት ዳግም ሀገር የመምራት ዕድል ማግኘቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅም እንደሚፈጥርለት ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የድርሻቸውን በመወጣት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም