አፋር-ለጥጥ ልማት የተመቸ ምድር - ኢዜአ አማርኛ
አፋር-ለጥጥ ልማት የተመቸ ምድር
ሰመራ፣መሰከረም 28 /2019 (ኢዜአ) ፡-አፋር-ለጥጥ ልማት የተመቸ ምድር
ኢትዮጵያ በተለያዩ የአየር ንብረት ቀጠናዎችና በተፈጥሮ ሀብት የታደለች በመሆኗ፣ ለተለያዩ የግብርና ምርቶች በተለይም ለጥጥ ልማት ከፍተኛ ምቹነት ካላቸው የዓለማችን አገራት አንዷ ናት።
አገሪቱ ያላት ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ተስማሚ የሙቀት መጠን እና በቂ የውሃ አማራጮች በጥጥ ምርት በስፋት ለመሰማራትና ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው አስፈላጊውን ጥሬ ዕቃ ለማቅረብም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ትልቅ እምቅ አቅምን ፈጥሮላታል።
ከእነዚህ ለጥጥ ልማት ከተመቹ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል የአፋር ክልል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በክልሉ ያለው ሞቃታማ የአየር ጠባይ እና የአዋሽ ወንዝ ለዘመናዊ የመስኖ ልማት ከሚሰጠው ሰፊ ዕድል ጋር ተደማምሮ፣ አፋርን የኢትዮጵያ «ነጭ ወርቅ» በመባል የሚታወቀው የጥጥ ምርት ዋና መገኛና እምብርት አድርጎታል።
ክልሉ ከሰው ዘር መገኛነቱ ባሻገር ለጥጥ፣ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች ልማት እንዲሁም የተለያየ የሰብል ዓይነትን ለማምረት የአየር ምቹ ሁኔታን የታደለ ነው።
የጥጥ ልማት ሲነሳ ቀደም ባሉት ዘመናት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ጥጥ እየተመረተ ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ሆኖ ያገለገለ ከመሆኑም በላይ፣ ጥጥ የዚሁ የበረሃው ምድር ዋነኛ መገለጫ በመሆን ይታወቃል።
ምርቱ ወደ አልባሳትን ለማምረት ዋነኛ ግብዓት በመሆኑ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ክልሉ ከፍተኛ የጥጥ ምርት እምቅ አቅምን የታደለ በመሆኑ ጥጥ ሲነሳ የአፋር ክልል አብረው የሚነሱ ናቸው።
በአፋር ክልል የሚለማው ጥጥ በመስኖ ሥራ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን፣ የታላቁ አዋሽ ወንዝን ዳርቻዎች በመጠቀምና በተመጋጋቢነት የሚከናወን ነው።
ጥጥ ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ በተለያዩ የውጭ አገራት ገበያ መፍጠር የሚችለውን ትስስር በማሳደግ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከርና ተወዳዳሪነትን ማዕከል ያደረገ ሥራ መስራት እንደሚገባ ይታመናል።
"ነጩ ወርቅ" በሚል ስያሜ የሚጠራውን ጥጥ፣ በአፋር ክልል አሁንም በስፋት ለማምረት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው መሆኑም ተመልክቷል።
በአፋር ክልል የጥጥን ምርት በማምረት ረገድ ያለውን አቅም በተመለከተ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሐመዱ መሐመድ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የአፋር ክልል መሬት ለጥጥ ልማት እጅግ የተመቸ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሰናዳው ጥናት በመነሳት እንደተናገሩት፣ በክልሉ ለጥጥ ልማት የተመቸ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይገኛል።
በዚህም መሠረት ማልማት በሚችሉ ወረዳዎች ላይ ሰብሉ እየለማ የሚገኝ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 21 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ሰብል መሸፈኑን አስረድተዋል።
የክልሉ የጥጥ ምርት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ከመሆኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ገበያም ጭምር ተፈላጊ መሆኑ ይታወቃል።
በሌላ በኩል 6ኛው ዓለም አቀፍ የጥጥ ቀን "ጥጥ ለበጎ፣ ለንግድ በትራንስፎርሜሽን አጋርነት ብልጽግናን መገንባት" በሚል መሪ ሐሳብ በኡዝቤኪስታን እየተካሄደ ይገኛል።
በዚሁ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የጥጥ እሴት ሰንሰለት ተጠቃሚዎች፣ አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ ባለፋብሪካዎች፣ ተመራማሪዎችና አጋር አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 70 በመቶ የሚሆነውን የጥጥ ገበያ የሚሸፍኑት ህንድ፣ አሜሪካና ቻይና መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።