ዓለም አቀፍ አድናቆት የተቸረው የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ አድናቆት የተቸረው የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር
አዲስ አበባ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ሳይንስ ዘርፍ በአፍሪካ ፋና ወጊ ስኬቶችን ማስመዝገቧ የሚደነቅ ነው ሲሉ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) አማካሪ ታካሺ ኦኢካዋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለአፍሪካ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም እንዳለውም አማካሪው ተናግረዋል።
የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ የፕሮጀክት ዋና አማካሪ እና የቦስተን ኮንሳልቲንግ ግሩፕ (BCG) ምስራቅ አፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ታካሺ ኦኢካዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ በዲጂታል ሽግግር ዙሪያ ከመንግሥት እና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ስታርትአፖች በቅርበት ለመሥራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ይህም በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ መሰረተ ሰፊ ለውጥ እየመጣ መሆኑን እንዲረዱ እንዳስቻላቸውም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስብስብ እና ለመስኩ እየተደረገ ያለው የመንግሥት ድጋፍ ሀገሪቱ ለአጠቃላይ በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንድታደርግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርላትም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ወጣትና ሊሰለጥን የሚችል እንዲሁም የቴክኖሎጂ እውቀትና ዝንባሌ ያለው የሰው ኃይል መኖሩ ለዘርፉ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አማካሪው አንስተዋል።
መንግሥት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ዲጂታል ሽግግር እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት አቅም ካለው የሰው ኃይል ጋር ተዳምሮ በቀጣይ ኢትዮጵያ በዲጂታል መስክ ተጠቃሽ ሀገር የሚያደርጋት መሰረት እየጣለ መሆኑን መገንዘባቸውንም ጠቅሰዋል።
"ይህ የወጣቶች አቅም እና የመንግሥት ድጋፍ ሲቀናጅ የኢትዮጵያ ዲጂታል ሽግግር በአስተማማኝ ምህዋር ውስጥ እንዲጓዝ የሚያደርግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአዲሱ የስታርትአፕ አዋጅ አማካኝነት ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚያደርገውን ማበረታቻ፣ ድጋፍ እና ስልጠና በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ዕድገት ለአፍሪካ ዲጂታል ሽግግር መሳለጥ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ያሉት አማካሪው ከራሷ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የዲጀታል አገልግሎቶችን የማቅረብ አቅም እየገነባች ነው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ማደግ ማለት የአፍሪካ ማደግ ማለት ነው" ያሉት አማካሪው፤ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ተዛማጅነት እና ተስማሚነት ያላቸውን አገልግሎቶች በማቅረብ፣ ሀገሪቱ የአገልግሎት ወጪ ንግዷን እንድታስፋፋ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ኦኢካዋ፤የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥራዎችን በተሳለጠ አግባብ እንዲመራ መደረጉ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚያመጣቸውን ዕድሎች በተጓዳኝ ስጋቶችንም የሚያስወግዱ ሥራዎችም አብረው ሊሰሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በሮቦቲክስ ዘርፍ ጠንካራ የቴክኖሎጂ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፊ እድሎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ጃፓን በሰው ሰራሽ አስትውሎትና በሮቦቲክስ ሰፊ ልምድ ያላት ሀገር መሆኑን ገልጸው፤እነዚህን ዘርፎች በማቀናጀት የላቀ ውጤት ለማምጣት ሀገራቱ ትብብራቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ጀማሪ ስታርትአፖችን የሚያበረታታ ፖሊሲዎችና አሰራሮችን እየዘረጋች መሆኑን ጠቅሰው፤ይህም በመሆኑን ወደ ፊት በመስኩ ትልቅ ውጤት ለማምጣት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።