ቀጥታ፡

አዲስ ከተመሰረተው የመደመር መንግስት ምን ይጠበቃል?

‎ሀዋሳ፤ መስከረም 28/2019 (ኢዜአ) - አዲስ ከተመሰረተው የመደመር መንግስት ምን ይጠበቃል?

የመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻልና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ ውጤትም አምጥቷል።

በዚህም ከተሞችን ለኑሮ፣ ለሥራና ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በሥራ ዕድል ፈጠራና በተከናወኑ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችም የህዝብን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል።

ህዝቡም በመንግስት የተጀመሩ የልማት፣ የሰላም፣ ሀገራዊ አንድነትና እድገትን የማምጣት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይሁንታውን ሰጥቶ የመንግስት ምስረታ ተካሂዷል።

አዲስ መንግስት መመስረቱን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር በሀዋሳ ከተማ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸው ሁለንተናዊ ስኬቶች የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች በአዲሱ መንግስትም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።     

ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል አቶ ብሩ ቢኖራ የመደመር መንግስት የለውጥ እሳቤና ተግባር በህብረ ብሔራዊነትና አብሮነት የጋራ ሀገር የመገንባት መሆኑን አሳይቶናል ብለዋል።

ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በህዝብ ተሳትፎ በቁርጠኝነት ሰርቶ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነፃና ፍትሐዊ ጠቅላላ ምርጫ መካሄዱ የዴሞክራሲ ዕድገት ማሳያ ነው ያሉት  አቶ ብሩ፣ በመደመር መንግስት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዳግም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለዘላቂ ሠላም፣ ሀገራዊ አንድነትና እድገት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ብሩ፣ በቀጣይ ለማከናወን የያዛቸው ሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በተለይ ሰላም ለሁሉም የልማት ዕቅዶች መሳካት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት በልዩ ትኩረት እንዲሰራበት የጠየቁት አቶ ብሩ፣ ሰላምን ማስፈን የሁሉም ሃላፊነት መሆኑንም አንስተዋል።  


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ተሾመ ላምቦሮ የመደመር መንግስት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ባከናወናቸው የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የህዝብን አመኔታ አግኝቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ህዝብና መንግስት የጀመሩት ብርቱ ጥረት ተጠናሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው፣ ለእዚህም ስኬት ሁላችንም ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ሙስናን ለመከላከል በመንግስት የተጀመሩ ሥራዎችም ውጤታማ እንዲሆኑ የህዝቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

ወጣት ብርሀን ሉቃስ በበኩሏ የመደመር መንግስት ከተሞችን ሳቢ፣ ለነዋሪዎች ምቹና የተሸለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብላለች።

ለአብነትም በሀዋሳ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ ዘመናዊነትን እንደትላበስ ማድረጉን ጠቅሳለች፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የህዝብ እርካታን ያሳደገ በጎ ጅምር መሆኑን ገልጻ፣ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ሥራዎች በቀጣይም መጠናከር አለባቸው ብላለች።

የከተማዋ ነዋሪዎች ባለፉት ዓመታት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች በአዲሱ የመደመር መንግስትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም