የመደመር መንግሥት የልማት ግቦች እንዲሳኩ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሚናቸውን ይወጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የልማት ግቦች እንዲሳኩ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሚናቸውን ይወጣሉ
ሮቤ፣ መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምሁራዊ ሚናቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ይህን የገለጹት በአዲሱ የመደመር መንግሥት የልማት አቅጣጫዎች፣ የሀገር ግንባታ ሂደትና የህዝብ ተጠቃሚነት ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህራንና ተመራማሪ አቶ ሌንጮ ሳሙኤል እንዳሉት፣ በልማት ሥራዎች የህዝብን ተሳትፎ በማረጋገጥ የአካባቢን ሀብትና አቅም ለልማት መዋል መንግስት ትኩረት የሰጠው ነው።
መንግስት ያስቀመጣቸው የልማት አቅጣጫዎችን ምሁራን በጥናትና ምርምር እና በሙያዊ ምክረሀሳብ በመደገፍ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመገንባትና በማጠናቀቅ ያሳየውን አቅም አጠናክሮ እንዲቀጥል ከምሁራን የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመደመር መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ለማፋጠን የያዘው ግብ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ሌንጮ የአገር ልማት ዘላቂ እንዲሆን የልማት ፕሮጀክቶች ከዜጎች ተጠቃሚነት ጋር ተያይዘው መተግበራቸው አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህም ምሁራዊ ድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አቶ ጉተማ አደም በበኩላቸው የመደመር መንግሥት በቀጣይ የሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት በዕውቀት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
የአገር ግንባታ ሂደት በመንግሥት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍ፣ ወጣቶችና መላው ህብረተሰብ የድርሻቸውን ሚና በተገቢው መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የሀገሪቱን የልማት ግቦች እውን ለማድረግ የሰው ኃይል አቅምን ማሳደግ፣ የትምህርትና የምርምር ሥርዓቱን ማጠናከር፣ የሥራ ፈጠራን ማበረታታት እና የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት።
ምሁራኑ የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን የያዛቸውን ግቦች እንዲሳኩ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ በምርምር፣ ሙያዊ ምክር በመስጠትና፣ በማስተማርና በማህበረሰብ አገልግሎት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የመደመር መንግሥት በቀጣይ የልማት ሥራዎችን ከማስፋፋት ባሻገር የልማት ትሩፋቶች በሁሉም ዜጎች ዘንድ እንዲደርሱ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሥራ ፈጠራና ከዜጎች የኑሮ መሻሻል ጋር እንዲገናኝ ይበልጥ አተኩሮ መስራት አለበት ሲሉም ምሁራኑ ጠቁመዋል።
በቀጣይ የሀገሪቱ የልማት ጉዞ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ሙያዊ አቅም ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ለዘላቂ ልማትና ለሀገራዊ ብልጽግና የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።