ቀጥታ፡

በክልሉ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር)

ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከወላይታ ዞን እና ወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ተወካዮች ጋር በቀጣይ ትኩረት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በመድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በክልሉ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት ይሠራል።


 

ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ለሕዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መሥራት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ገልፀው በክልሉ ያሉትን የመልማት አቅሞች በመጠቀም ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት በቅንጅት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ላይ በውጤታማነትና በቅንጅት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የወላይታ ሀገር ሽማግሌ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ፣ በዞኑ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል።


 

ለሁሉም ልማት መሠረት የሆነው ሰላምና አንድነት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አንስተው የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

መጋቢ ዮሐንስ ባሳና (ዶ/ር) በበኩላቸው አዲሱ አመራር የሕዝቡን ጥያቄ በቅርበት በመከታተል የመመለሱ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።

የወላይታ ዞን ወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ታደለ ሜጋ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስቷል።


 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ ኤልያስ በበኩላቸው በሕፃናትና ሴቶች ሕገወጥ ፍልሰት ቁጥጥር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በኑሮ ውድነት ቅነሳ እና በስብዕና ማዕከል ግንባታ ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።


 

በወቅቱ ከሁሉም አካላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በርዕሰ መስተዳድሩና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ምላሽ ከተሰጠ በኋላ  በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያም ምክክር በማድረግ ውይይቱ ተጠናቋል።

በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም