ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃደኝነት በሚለገስ የሚተካ ደም የማይተካውን የሰዎች ህይወት እንታደግ

ደሴ፣ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፡-በበጎ ፈቃደኝነት በሚለገስ የሚተካ ደም የማይተካውን የወገኖቻችንን ህይወት እንታደግ ሲሉ ለበርካታ ጊዜያት ደም የለገሱ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አገልግሎቱ ከበጎ ፈቃደኞች ተጨማሪ ደም ለመሰብሰብ የሚያስችለውን የግንዛቤ ማሳደጊያ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት መምህር ኑሩ ይመርና ወጣት ሰሚራ ሰይድ፤ በበጎ ፈቃደኝነት በሚሰጥ የሚተካ ደም የማይተካውን የወገኖቻችንን ህይወት እንታደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መምህር ኑሩ ለ92 ጊዜያት ደም በመለገስ፣ በደም እጦት ለሞት አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን መታደግ በመቻላቸው ሁልጊዜም የሕሊና እርካታና ደስታ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል። 


 

መምህር ኑሩ አክለውም ሦስት ልጆቻቸው አርአያነታቸውን በመከተል ቋሚ ደም ለጋሽ ሆነው በርካታ ወገኖችን በደም እጦት ምክንያት ከመሞት እየታደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ደም መለገስ የሚያስከትለው ምንም ዓይነት ጉዳት ስለሌለው በደም እጦት ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ሕይወት መታደግ አለብን ያለችው ደግሞ ወጣት ሰሚራ ሰይድ ናት። 

እርሷም በቋሚነት ደም እየለገሰች መሆኑን ጠቁማ፣ ጓደኞቿን በማስተባበር በየሦስት ወሩ በቋሚነት ደም እንዲለግሱ የማድረግ ተግባሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጣለች።


 

የደሴ ደምና ሕብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ታደሰ ሲሳይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ በቀላሉ የሚተካውን ደም በመለገስ የማይተካውን ክቡር የሰው ሕይወት እንደመታደግ ትልቅ ነገር የለም። 

እስካሁን በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በሚሰበሰበው ደም የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የተሰበሰበውን 11 ሺህ 778 ዩኒት ደም ለ36 የጤና ተቋማት በማሰራጨት፣ በአደጋና በወሊድ ጊዜ ደም ፈሷቸው ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የደረሱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል። 

በጎ ፈቃደኞች በለገሱት ደም የበርካታ ዜጎች ሕይወት መታደግ መቻሉን የጠቀሱት ኃላፊው፣ አሁንም በጎ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። 

በዘንድሮው በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 15 ሺህ 515 ዩኒት ደም ውስጥ እስካሁን ከ5 ሺህ ዩኒት በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።


 

የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው በትራፊክ አደጋ፣ በወሊድና በሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ደም ፈሷቸው በደም እጦት የሚሞቱ ዜጎችን ለመታደግ ከስጦታ ሁሉ የሚበልጠውን ደም በመለገስ ሁሉም ማኅበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። 

በዞኑ በተለያዩ ተቋማት አማካይነት ሕብረተሰቡን በማስተባበር ደም እንዲለግስ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በመድረኩም ከደቡብ ወሎ ዞን፣ ከደሴ ከተማ፣ ከወረዳዎችና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮች፣ ደም ለጋሾችና ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም