ቀጥታ፡

በክልሉ የህክምና አገልግሎትን ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ደብረ ብርሃን፤ መስከረም 27/ 2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሕክምና አገልግሎትን ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሠራሮች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሐኪም ግዛው ሆስፒታል የሲቲ ስካን (CT Scan) እና የፍሎሮስኮፒ (Fluoroscopy) ሕክምና ቴክኖሎጂዎች ዛሬ ሥራ ጀምረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሕክምና አገልግሎት ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው።


 

በተለይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሠራሮች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ ለማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የጀመራቸው ተግባራት በተለይ አክሞ ከማዳን አንፃር ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን እንግልትና ወጪ ለመቀነስ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።

ይሕም የአካባቢውን ሕዝብ ጨምሮ ከአፋርና ከኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ለሚመጡ ዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋፋት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ አዳዲስ የሕክምና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ለሚመጡ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችና ማበረታቻዎች እንደሚያቀርብም አመልክተዋል።

የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።


 

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለስ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ አልሞ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት አገልግሎቱ ምቹ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም