የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባርን ለመወሰን የጸደቁ አዋጆች የተቋማትን የማስፈጸም አቅም የሚያልቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባርን ለመወሰን የጸደቁ አዋጆች የተቋማትን የማስፈጸም አቅም የሚያልቁ ናቸው
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የጸደቁ አዋጆች የተቋማትን የማስፈጸም አቅም የሚያልቁ መሆናቸውን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባውን ዛሬ ያካሔደ ሲሆን፤ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፤ አዋጁ የአስፈፃሚ አካላትን የወልና የተናጠል ተግባራት በግልጽ በማስቀመጥ ውጤታማ አደረጃጀት ለመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አዋጁ የተቋማትን ስልጣንና ተግባር ተገማች የሚያደርግ፣ አዳዲስ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስችልና የአንዳንዶቹን ስያሜ የሚለውጥ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና ሃና አርአያሥላሴ የአዋጁን አስፈላጊነትና ዓላማ አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል።
የአዋጁ መውጣት ባለፉት አምስት ዓመታት በአስፈጻሚ ተቋማቱ የታዩ ውስንነቶችን በማቃለል የዜጎችን መብት ለማስከበር፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥና የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ይረዳል።
በተጨማሪም አዋጁ በሰፊ ጥናትና ከሚኒስቴር በተገኙ በቂ ግብዓቶች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ አደረጃጀቱና የተደረጉት የስያሜ ማሻሻያዎች ተቋማቱ ተልዕኳቸውን እንዲያጠናክሩና ግልጽ፣ አጭር እንዲሁም አቃፊ እንዲሆኑ ታሳቢ ተደርጓል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ሃና አርአያሥላሴ በበኩላቸው፤ አዋጁ የሀገሪቷን ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ያከበረ፣ በጥናትና በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተደገፈ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ረቂቁ ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሙ ውስንነቶችን የሚያርም እንዲሁም በተቋማት መካከል ግልጽ የሥራ ክፍፍልና ቅንጅት እንዲኖር እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት ረቂቅ አዋጁ ቀልጣፋ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማስፈጸም አቅም እንደሚያሳድግና የተጠሪ ተቋማት ለውጥ የስራ ባህሪያቸውን ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባል ፈቲህ መሃዲ (ዶ/ር) አዋጁ የመደመር ስትራቴጂካዊ እሳቤን የሚያሳካና በሁሉም መስክ ሀገራዊ እድገትን የሚያፋጥን ትልቅ ሰነድ መሆኑን አብራርተዋል።
የምክር ቤት አባል አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፤ አዋጁ የተቋማት ሥልጣንና ተግባር እንዳይደራረብ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅም በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡