ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ሆኗል

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሆነ ታላቅ ተግባር መሆኑን የዘርፉ ሙያተኞች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይን አንግባ በትኩረት እየሰራችባቸው ከሚገኙ ውጤታማ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አረንጓዴ ዐሻራ አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትን ለመከላከል፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በአርንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ተክላለች።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን መካሄዱ ይታወቃል።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 56 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶችን አረንጓዴ ማልበስ ተችሏል።

በተጨማሪም ይህ መርሀ ግብር የመሬት መሸርሸርን እንዲቀንስ፣ ስነ ምህዳራን መጠበቅ እንዳስቻለም መግለጻቸው ይታወሳል።

በተባበሩት መንግስታት የደን ፎረም ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ዶክተር ጁሊያት ቢያኦ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የደን ሽፋንን ለመጨመር የሚከናወኑ ተግባራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል።

የደን መራቆትን ለመቅረፍና የመሬት ገጽታ ለመጠበቅ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የዘርፉን ተዋንያን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን ነድፎ ባለፉት ዓመታት በመተግበር የአረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግ ያከናወነው ተግባር ውጤት ማስመዝገቡንም አክለዋል።


 

የአፍሪካ የደን ፎረም የደን ተመራማሪ የሆኑት ዶሪስ ሙታ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአካባቢ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያከናወነቻቸው ውጤታማ ተግባራት ከደን ሽፋን  መመናመን ጋር ተያይዞ  የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትን በመከላከል በኩል ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ያስመዘገበችው ውጤት በዘርፉ በትኩረት ከተሰራ ታሪክ መቀየር እንደሚቻል ለዓለም ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።

እንደ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አይነት ፕሮጀክት ነድፎ መተግበር ፋይዳው አካባቢን በደን ከመሸፈን በላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም መሰል ምሳሌ የሚሆን ተግባር ሰዎች በምቹ ስነ ምህዳር እንዲኖሩ ዕድል የሚፈጥርና ምርታማነትን የሚያሳድግ አርዓያነት ያለው ተግባር እንደሆነም ነው ዶሪስ ሙታ ( ዶ/ር) የገለጹት። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም