ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች የወጣቶችን በሀገራቸው ሰርተው የመለወጥ ተስፋን በእጅጉ የሚያለመልሙ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ 

በዚህም ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለሁለተኛ ጊዜ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ሁሉም ዜጎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች አባቶችና እናቶች ለሀገር እድገትና አንድነት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ መዘጋጀት እንዳለበትና የዛሬ ወጣቶች በሩቅ አሳቢነት ነጋቸውን እንዲቀርጹም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ወጣቶችን በተመለከተ ያስተላለፉትን መልዕክት መነሻ በማድረግ ኢዜአ የአዲስ አበባ ወጣቶችን አነጋግሯል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደገለጹት የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሰጠው ልዩ ትኩረት የሚደነቅ ነው፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ኢክራም አበራ እንደገለጸችው፤ የመደመር መንግሥት እንደአጠቃላይ ለሀገር ልማት እና ዕድገት ያስቀመጣቸው አዳዲስ አቅጣጫዎች ትልቅ ርዕይና ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል፡፡

በተለይ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የሰጠው ትኩረትና ያስቀመጠው አዲስ አቅጣጫ የወጣቱን በሀገሩ ሰርቶ የመለወጥ ተስፋ በእጅጉ ያለመለመ መሆኑንም ተናግራለች። 

መንግሥት ወጣቱ በስራና ክህሎት አቅሙን አጎልብቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ለማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙትን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት ጠቁማ፤ እኛ ወጣቶችም ለዚህ ሀገራዊ ስኬት ሀላፊነታችንን እንወጣለን ብላለች፡፡


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ማስረሻ ሀይሌ አዲስ የተመሰረተው የመደመር መንግሥት ያስቀመጣቸው የልማት አቅጣጫዎች ሀገርን የሚያሻግሩ እና ዕድገቷን የሚያፋጥኑ ናቸው ብሏል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር የወጣቱን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት የያዘውን ዕቅድ በግልጽ በማቅረባቸው ተደስቻለሁ ነው ያለው።

መንግስት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በግልጽ ማቅረቡ ወጣቶችም ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላል ሲል ገልጿል።       

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እንደሚከናወኑ በመግለጻቸው ተደስቻለሁ ብሏል፡፡

የመደመር መንግሥት የወጣቶችን በሀገራቸው ሰርቶ የመለወጥ ተስፋ አሳድጓል ያለችው ደግሞ ወጣት ፍጹም አምሳሉ ናት። 


 

ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በትብብር በመስራት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግራለች።

እኛም መንግሥት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ላይ በንቃት መሳተፍ ይገባናል ብላለች፡፡

ወጣት ተስፋዬ አወቀ በበኩሉ፤ በሀገሪቷ እየተገነቡ የሚገኙትና በቀጣይም ለመገንባት በዕቅድ የተያዙ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በቀጥታ ወጣቶችን የሚያሳትፉ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ወጣቱ አቅሙን ማጎልበትና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ሲል ገልጿል።


 

እንደወጣትም በሀገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙትን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍም ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅብናል ነው ያለው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም