ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከሀገሪቱ ባለፈ የቀጣናውን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ናቸው - አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከሀገሪቱ ባለፈ የቀጣናውን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ናቸው ሲሉ በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን ገለጹ። 

አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሜጋ ፕሮጀክቶች ለሀገሪቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት ወሳኝ ከመሆናቸው ባሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት፤ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በመሰነቅ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ልማቷን ለማስቀጠል እንዲሁም ይህን ፈጣን ልማት ለማሳለጥ የባህር ባለቤትነቷን ለማስመለስ በትጋት እየሰራ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ማካሄዱ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሰየመ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ብሎም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እና በትጋት እንደምትሠራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አርሜኒያ እንደ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር በመሆኗ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ አስፈላጊነት ትገነዘባለች።

የባህር በር ማግኘት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት እና ልማትን ለማፋጠን አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ በተለይ በርካታ የሕዝብ ብዛትና ሰፊ የቆዳ ስፋት ላላት ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግን መሰረት በማድረግ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አርሜንያ እንደምትደግፍም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነች መሆኑን አንስተው፤ እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ልማት መፋጠን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንዱ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራትና ህዝቦች ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግንባታ በሀገሪቷ እየተከናወኑ ከሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት አየር መንገዱ በዘርፉ ያለውን የመሪነት ሚና ያጠናክራል ብለዋል።  

አምባሳደሩ አክለውም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከሀገሪቱ ባለፈ የቀጣናውን እንዲሁም የአፍሪካን ሀገራት እና ህዝቦች ተጠቃሚነት የሚያጎለብት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም