የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በጊዜ የለንም መንፈስ እንሰራለን-ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በጊዜ የለንም መንፈስ እንሰራለን-ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በጊዜ የለንም መንፈስ እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ተናገሩ።
አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ ሥራቸውን በይፋ ሲጀምሩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ርዕስ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህዝቡ የሰጠን አደራ በማክበርና የገባነውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር በጊዜ የለንም መንፈስ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በክልሉ መንግስት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆኑ በተቀናጀ መልኩ ይሰራል ብለዋል።
የጋራ ትርክትን በመገንባትና የክልሉን ህዝብ አብሮነት በማጠናከር ልማትን የማፋጠን ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑንም ርዕስ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የልማት ጸጋ፣ ልምድና የህዝብን የጋራ አሴቶች በማቀናጀት በተደመረ አቅም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ህዝብን በትጋትና በቁርጠኝነት በማስተባበር የመሪነት ሚናውን በብቃት እንዲወጣ አሳስበዋል።
ህዝቡን ያላሳተፈ ልማት ስኬታማ እንደማይሆን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።