የኢትዮጵያ የተስፋ መንገድ፤ ከምርጫ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተስፋ መንገድ፤ ከምርጫ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖት
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተስፋ መንገድ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን፣ የኢኮኖሚ ልማትንና የሀገር አቅም ግንባታን በማጠናከር ወደ ዘላቂ ልማት የሚያመራ ጉዞ መሆኑን ነጋሪ መጽሔት ዳሰሰች።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የምትታተመው ነጋሪ መጽሔት ''የኢትዮጵያ የተስፋ መንገድ'' በሚል ዐበይት ርዕስ፤ ከምርጫና ከዴሞክራሲ ግንባታ ጀምሮ የሀገሪቱን የለውጥ ፍኖትና ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ ዳስሳለች።
መጽሔቷ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ የታየበትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አብራርታለች።
የ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፎና ዜጎች ከሌሊት እስከ ሌሊት ድምፃቸውን መስጠታቸውን በማንሳት፣ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳሳለች።
«ነጋሪ» በዚሁ አምዷ ዴሞክራሲ በምርጫ ቀን ብቻ የሚገነባ ሳይሆን በጠንካራ ተቋማት፣ በሕግ የበላይነትና በንቁ ዜጎች ተሳትፎ የሚጠናከር የረጅም ጊዜ ጉዞ መሆኑን ትገልጻለች።
በዚህም የሕግ የበላይነትን ከፖለቲካ ፍላጎት በላይ ማስቀመጥ፣ የፖለቲካ ውይይትና መቻቻልን ማጠናከር፣ እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ውጤቶችን ወደ ተግባር መቀየር እንደ ቀጣይ የቤት ሥራ አስቀምጣለች።
በኢኮኖሚው ዘርፍም የሀገሪቱን የመቻል አቅም ማሳደግና ''ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል'' መሸጋገር የተስፋው መንገድ አንዱ መሠረታዊ አቅጣጫ መሆኑ ተዳሷል።
በዚህ ማዕቀፍም የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የምርት አቅምን ማጎልበት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሳለች።
በተለይ ''ኢትዮጵያ ታምርት'' የተሰኘው አገር በቀል ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ የሚያበረክተው ሚና ተብራርቷል።
በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከ11 በመቶ በታች መሆኑን በማንሳት፣ ይህንን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዋነኛ መዋቅራዊ ግብ መሆኑን አብራርታለች።
ግብርናን ወደ ዘመናዊና ዲጂታል ሥርዓት ማሸጋገርም በተስፋ መንገዱ ውስጥ ተጠቃሽ መሆኑ ተዳሷል።
የገበያ መረጃ፣ የአርሶ አደሮች ምዝገባ፣ የግብዓት ሥርጭትና የፋይናንስ ተደራሽነት በዲጂታል ሥርዓት መደገፋቸው፣ የሳተላይት መረጃና ዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት መጠቀም እንዲሁም የዲጂታል አርሶ አደር ምዝገባ ሥራዎች ዘርፉን ወደ ዘመናዊ አሠራር እያሸጋገሩት መሆኑ ተገልጿል።
በውጭ ግንኙነት በኩልም የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የወደፊት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የንግድ ተወዳዳሪነትና የቀጣናዊ ትስስር ስትራቴጂካዊ ጉዳይ መሆኑ ተብራርቷል።
ነጋሪ ይህንን ከዘመናዊ ዲፕሎማሲ አቅጣጫ ጋር በማስተሳሰር፣ ኢትዮጵያ ከባህላዊ ዲፕሎማሲ ወደ ፈጠራና ቴክኖሎጂን ወደሚያካትት አቀራረብ እየተሸጋገረች መሆኗን ዳስሳለች።
በተጨማሪም የብሪክስ አባልነት ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ድጋፍ የሚያደርግ ስትራቴጂካዊ መንገድ መሆኑን በማንሳት፣ ውጤታማነቱ በተቋማዊ አቅምና በውጤታማ ዲፕሎማሲ እንደሚረጋገጥ አመልክታለች።
በአጠቃላይ ነጋሪ የዚህን ዕትም ዋና ጉዳይ በማድረግ የዴሞክራሲ ግንባታን፣ የተቋማትን ጥንካሬ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን፣ የኢንዱስትሪና ግብርና ልማትን እንዲሁም የባሕር በርና የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎችን በማያያዝ የሀገሪቱን የተስፋ መንገድ አስቃኝታለች።
የመጽሔቷ ዋና አምድ በተጨማሪም በምርጫ፣ በለውጥና በልማት የተገኙ ልምዶችን ወደ ቀጣይ የሀገር ግንባታ ሥራ መቀየር የሚለውን መልዕክት አጽንኦት ሰጥቶታል።
የአሁኑ ዕትም በዚህ ዋና አምድ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጤና ነክ ጉዳዮችንም የያዘ ሲሆን፣ በዕትሟ የተካተቱትን ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች አንባቢዎች መጽሔቷን በማንበብ ማግኘት ይችላሉ።
የነጋሪ መጽሔት አዲሱንና ነባሩን ዕትሞች የዲጂታል አማራጭ ይጎብኙ
https://www.ena.et/web/negari/home