የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባኤዎች የሥራ ርክክብ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባኤዎች የሥራ ርክክብ አደረጉ
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባኤ በመሆን የተመረጡት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከቀድሞው የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር የሥራ ርክክብ አከናውነዋል።
በርክክቡ ወቅት አዲሷ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የጀመራቸውን ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች አጠናክሮ በመቀጠል፣ ተቋሙ የተጣለበትን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት በብቃትና በጥራት እንዲወጣ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አክለውም ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥቱን መርሆች በማስከበር፣ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ጉዳዮችን በሕጋዊና በተቋማዊ አግባብ ለመፍታት የሚያስችለውን አቅም በመገንባት ጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት እንዲገነባ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ በመሆን የተመረጡት አቶ ደስታ ሌዳሞ ከቀድሞዋ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዛሀራ ሁመድ ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል።
አቶ ደስታ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ የተጣሉበትን ከፍተኛ ብሔራዊ ተልዕኮዎች በብቁ ትጋትና በቁርጠኝነት ለማሳካት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች እሴትና አብሮነት የሚያጠናክሩ፣ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ መግባባትንና ሰላምን የሚያሰፍኑ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቀድሞው ምክር ቤት የተጀመሩ በጎ ተነሳሽነቶችና አበይት ተልእኮዎች በተቀናጀ መልኩ እንደሚቀጥሉ መረጋገጡን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።