በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በተቀናጀ መልኩ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በተቀናጀ መልኩ ይሰራል
ሆሳዕና፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።
አዲስ የተሾሙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)፤ ከቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል።
ርእሰ መስተዳደር የትምጌታ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የመደመር መንግስት የሚያቅዳቸውን በማሳካትና የጀመራቸውን በማጠናቀቅ ሰፊ ልምድ ማካበቱን አስታውሰዋል።
በዚሁ መሰረትም የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በተቀናጀ መልኩ ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የህዝቡ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉን ህዝብ ትብብርና አብሮነት ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ትርክትን መገንባትና ልማትን ማሳካት ዋነኛ ግባችን ይሆናል ብለዋል።
የህዝብ አደራ የአመራሩን ትጋትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ከባድ ሃላፊነት መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በላቀ ብቃት ለመወጣት አቅምን በማካበት በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማስቀጠልና በቅብብሎሽ ለህዝብ ተጠቃሚነትና ለክልሉ ልማት በትብብርና መደጋገፍ መስራታችን ይቀጥላል በማለት ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድር መልካም የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ዲላሞ አቶሬ (ዶ/ር) ፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።