ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው ነው ያፀደቀው፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ግልጽና ውጤታማ የሆነ የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት በመፍጠር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የተጠሪ ተቋማት የውልና የተናጠል ተግባር በግልጽ በማስቀመጥ ረገድ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ተወካዮች የሆኑት ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና ሃና አርአያሥላሴ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት እና ዓላማ በተመለከተ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል።
በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት መስሪያ ቤቶች በአለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የታዩትን ውስንነቶች ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ እና የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲአዊ መብቶች እንዲከበሩና የህዝቡ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እና የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ጥናት የተደረገበት እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ግብአት ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የተቋማትን አደረጃጀት በግልጽ ማስቀመጥ የመንግስትና የህዝብ ሃብት የስራ ኃላፊዎች በአግባብ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ አንዳንድ የተጠሪ ተቋማት ለውጥ በደንብ የስራ ባህሪያቸውን እና ያላቸውን ፋየዳ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቀልጣፋና ውጤታማ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን የምክር ቤት አባላቱ ጠቁመዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው፤ ፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት ፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1440/2019 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡