የመደመር መንግሥት ያቀዳቸው ግቦች ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ ያረጋግጣል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ያቀዳቸው ግቦች ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ ያረጋግጣል
አርባ ምንጭ/ጂንካ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ያቀዳቸው ግቦች ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ ያረጋግጣል ሲሉ የአርባ ምንጭ እና የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የእድገት ጉዞ ያፋጠነና ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎችን አከናውኗል።
እነዚህ የልማት ሥራዎቸ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጹን ለብልፅግና ፓርቲ በመስጠት ከመንግስት ጎን መሆኑን አረጋግጧል።
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባም አዲሱ የመደመር መንግስት የተመሰረተ ሲሆን ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በድጋሚ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎም ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን፤ መንግስታቸው ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በፓርላማ ንግግራቸው አረጋግጠዋል።
ይህን ተከትሎ ኢዜአ በአርባ ምንጭና በጂንካ ከተሞች ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ተጠቃሚ መሆናቸውንና ይህንንም ለማጠናከር ከመንግስት ጎን እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።
ከአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሰላምነሽ አትርሳው እንዳሉት የመደመር መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ያደረገ ነው።
አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በመሶብ የአንድ ማዕከል የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች የነዋሪውን እንግልት ያስቀሩ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በሌማት ትሩፋትም በርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
የመደመር መንግስት ዳግም ሀገር የመምራት ዕድል ማግኘቱ እነዚህን የልማት ተግባራት ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ ያቀደውን የማሳካት ጠንካራ አቅሙ የልማት ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ ያሳድገዋል ብለዋል።
ወጣት አብርሃም መስፍን እና አቶ ተገኝ ታደሰ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ አርባ ምንጭ ከተማ እንድታንሠራራ ማድረጉን ተናግረዋል።
መንግስት የጀመረውን የመጨረስ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል ያሉት ነዋሪዎቹ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በጂንካ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ የመደመር መንግስት በድጋሚ ሀገር የመምራት ዕድል ማግኘቱ በየዘርፉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር መንግስት ያቀዳቸውን ግቦች ማሳካት የሚችል ጠንካራ አቅም ያለው በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ያረጋግጣል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ከነዋሪዎች መካከል ወጣት ተመስገን እርገዶ እና ትንሳኤ ኃይሉ፤ የመደመር መንግስት ኢትዮጵያን የሚያሻግር የልማት ውጥን ያለው እና ቃሉን በተግባር እንደሚፈጽም በተደጋጋሚ ያሳየ መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችም የመንግስት ጥንካሬ ማሳያ መሆናቸውን አንስተዋል።
አቶ ይበልጣል አባይነህ የተባሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ የትውልድ የዘመናት ጥያቄ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ከዳር እንዲደርስ የተጀመሩ ጥረቶችና የተመዘገቡ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብለዋል።