ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ

ደሴ ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ይከናወናሉ ሲሉ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ገለጹ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ እንደገለጹት፣ የከተማውን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል ነዋሪውን ይበልጥ ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ተይዟል።

አስተዳደሩ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለከተማ ግብርና፣ ለሌማት ትሩፋት፣ ገበያን ለማረጋጋት፣ ለኮሪደር ልማትና ለሌሎች ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የልማት ግቦችን ለማሳካትም ከባለሃብቶች፣ ከነዋሪዎች እና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተማዋን የበለጠ ውብና ሳቢ በማድረግ ለነዋሪዎች፣ ለጎብኝዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ስራ በቁርጠኝነት እንደሚከናወንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።

አስተዳደሩ የያዛቸውን የልማት ግቦች በገንዘብና በጉልበት በመደገፍ ለከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት ስራ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋነህ ነጋ እና ወይዘሮ መቅደስ ገብረማሪያም ናቸው።

በከተማዋ ተግባራዊ በተደረጉ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አመልክተው በዘንድሮው ዓመትም የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ከአስተዳደሩ ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም