"የነጭ ወርቅ" ጸጋና በረከት - ኢዜአ አማርኛ
"የነጭ ወርቅ" ጸጋና በረከት
ገንዳውኃ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ "የነጭ ወርቅ" ጸጋና በረከት፤ የኢኮኖሚ ምንጭና የስልጣኔ መገለጫ
በአለም ላይ የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረው በጨርቃ ጨርቅና ሱፍ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።
በ18ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ የተቀሰቀሰው የኢንዱስትሪ አብዮት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል የጥጥ ማቀናበሪያ ማሽኖችና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች መከፈት ነበር።
በእንግሊዝ የተቀጣጠለው የጨርቃጨርቅና የሱፍ ኢንዱስትሪ አብዮት የሰብል ልማት የሚካሄድበትን መሬት ወደ በግ ፣ግጦሽና ጥጥ ልማት በመቀየሩ "በጎች ሰዎችን እየበሉ ነው" ብሎ በመጻፍ ታዋቂው ጸሃፊ ቶማስ ሙር መቃወሙ ይታወሳል።
በአገራችን ኢትዮጵያም እንደ አፋር፣ የአማራ ክልል ሰሜን ምእራብና ምእራብ ቆላማ አካባቢዎች የጥጥ ምርት በስፋት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ግብአት በመዋል የአገራችን እድገት እንዲፋጠን በማስቻል የሚታወቁ ናቸው።
በምእራብ ጎንደር ዞን በኢትዮጵያ የጥጥ ምርት ታሪክ ቀደምትና የጥጥ ምርት መገኛ ዋና ማዕከል በመሆኑ ከሚያስገኘው ጥቅም በመነሳት የአካባቢው ህዝብ ጥጥን “ነጩ ወርቅ” እያሉ ይጠሩታል።
ዞኑ ለሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ ቦሎቄና ሌሎች የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙና ለኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚውል ተኪ ምርቶችን በስፋት በማምረት ለአገራችን ልማት የጀርባ አጥንት ነው።
ለገበያ ተኮር ምርቶች ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ምቹ ስነ ምህዳርና የአየር ንብረት፣ እምቅ የውሃ ሃብት ያለው በመሆኑ ለመካናይዜሽን የግብርና ልማት የተመቸ ነው።
ምንም እንኳ ዞኑ ለተኪ ምርትና ለወጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶች ያለው ጸጋ ከፍተኛ ቢሆንም የዛሬው የጽሁፍ መነሻ “6ኛውን የዓለም የጥጥ ቀን (World Cotton Day)” አስመልክቶ በጥጥ ልማት ላይ ያጠነጠነ መሆኑ አልቀረም።
ያለውን የጥጥ ልማት ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የዞኑ አርሶ አደሮችና ከአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ባለሃብቶች የጥጥ ልማትን በስፋት እያካሄዱ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በዞኑ ከ300 በላይ ባለሃብቶች እና ከ10 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በየዓመቱ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ በማልማት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ ያቀርባል።
ከእርሻ እስከ ጥጥ መዳመጫና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች፣ ከማከማቸት፣ ማጓጓዝና ወደ ውጭ መላክ ያለው የንግድና የእሴት ሰንሰለት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ለአገር በሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬና ለህብረተሰቡ በሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም “ነጩ ወርቅ” ተብሎ ለመጠራት በቅቷል።
በዞኑ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎችና የምርጥ ዘር አቅርቦት መስፋፋት በዘርፉ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል።
የጥጥ ምርት የኢኮኖሚ መሠረት ብቻ ሳይሆን የአገራት የጥበብ፣ የባህልና የስልጣኔ መገለጫና ማስተሳሰሪያም ጭምር መሆኑን የኢትዮጵያን የሸማ፣ የጥበብና የባህል አልባሳት በዓለም ደረጃ ያለውን ተወዳጅነት ማየት በቂ ነው።
በጥጥ የተሰሩ ባህላዊ አልባሳት የህብረተሰቡን ውበት፣ ታሪክና ጥበብ የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው የማንነት መግለጫም ጭምር ነው። በኢትዮጵያውያን እናቶች ውብ እጆች ተፈትሎ፤ ድርና ማግ ተሰናስሎ በመሸመን በባህላዊ እንዱስትሪ የሚመረተው የባህል አልባሳት ዛሬ የአገራችን መገለጫ ለመሆን በቅቷል።