ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካሔደ መሆኑን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ በዘመናዊና ባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል።


 

በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በሚገኙ 15 ወረዳዎች የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በተቀናጀ አግባብ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

መንጋው የማሽላ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የገብስ፣ የዳጉሳ፣ የሩዝ እና የመሳሰሉ ሰብሎችን በእሸትነት ደረጃ ፍሬውን በመብላትና በማራገፍ ጥፋት የሚያስከትል ነው።

በዚህም 74 የግሪሳ ወፍ መንጋ ማደሪያ ቦታዎችን በመለየት ከመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በማከናወን አብዛኛውን የግሪሳ ወፍ ማስወገድ ተችሏል።


 

በተቀናጀ መንገድ በተካሄደ የመከላከል ሥራ ሰብሉን ሙሉ በሙሉ ከግሪሳ ወፍ ጉዳት መታደግ እንደተቻለ ነው ዳይሬክተሩ ያስገነዘቡት።

አርሶ አደሩ በየእለቱ ሰብሉን አሰሳ በማድረግ ከግሪሳ ወፍ ጉዳት የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ከበደ በበኩላቸው፤ መንጋው የተከሰተው በከሚሴ ከተማ አስተዳደር፣ በዳዋ ጨፋ፣ በአርጡማ ፉርሲ፣ በጅሌ እና ባቲ ወረዳዎች መሆኑን ተናግረዋል።

መንጋውን በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ፈጥኖ በማከናወን የመከላከል ሥራ በመሠራቱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የግሪሳ ወፍ ማስወገድ መቻሉን ገልጸዋል።

አሁንም መንጋውን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው፤ አርሶ አደሩም በባህላዊ መንገድ ድምፅ በማሰማት መንጋው በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም