ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት በየደረጃው ለሚፈጽማቸው የልማት ፕሮጀክቶች መሳካት የበኩላችንን እንወጣለን

ባህርዳር፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት በየደረጃው ለሚፈጽማቸው የሰላምና የልማት ፕሮጀክቶች መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የመደመር መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በጥራት በመፈፀሙ የኢትዮጵያን ዕድገት ለማፋጠን በቁርጠኝነት በመሥራቱ ዳግም እንዲመረጥ አስችሎታል።

ያካበተውን የልማት ልምድ በመጠቀም በቀጣይ የላቀ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ሞላ ካሳ እንደገለጹት፤ የተመሠረተው አዲሱ የመደመር መንግሥት የሚስተዋሉ ችግሮችን በሠለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ መፍታቱን ይቀጥላል የሚል እምነት አላቸው።

የኮሪደር ልማትን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች በማስፋት፣ የተጀመሩ ግዙፍ የማዳበሪያ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የጋዝ ማውጫ እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ዳር በማድረስ ዕድገታችንን እንደሚያፋጥን እንጠብቃለን ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ያጣችውን የባሕር በር ሰጥቶ በመቀበል መርህ በማሳካት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራቱን መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ የምሥራች አበጀ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት ሰላምን ለማጽናት የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። ለስኬቱም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል የሀገሪቱን ዕድገት እንዲያፋጥን ጠይቀዋል፡፡

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በማረምና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘለቀ ገበየሁ ናቸው።

ገዥ ትርክቶችን በማስረጽና በዚሁ ላይ የተመሠረተውን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ማጠናከር  ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የመደመር መንግሥት አቅዶ በየደረጃው ለሚፈጽማቸው የሰላምና የልማት ፕሮጀክቶች መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም