ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለጤናማና ምርታማ ትውልድ ጠንካራ መሠረት ለመጣል በቁርጠኝነት ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለጤናማና ምርታማ ትውልድ ጠንካራ መሠረት ለመጣል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣የአፍሪካን ነገ ለመቀየር የሕጻናትን ጤና ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክን ከናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ እና ከፍተኛ ልዑካናቸው ጋር በመሆን በይፋ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሣሠሩ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ሰፊ የሕዝብ፣ የሰው ሀብትና የኢኮኖሚ ዐቅም በተቀናጀ ጥረት ሲመራ ለአፍሪካ ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

ናይጄሪያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ያመጣነውን ተጨባጭ ተሞክሮ ለመቅሰም ያደረገችው ጉብኝትም የዚህ አጋርነት ተጨባጭ መገለጫ መሆኑን አመልክተዋል።

ሥርዓተ ምግብ የጤና ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሰው ሀብት ልማት፣ የትምህርት ውጤት፣ የምርታማነት ዐቅምና የወደፊት ብልጽግና መሠረት ነው።

ስለዚህ የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ በከፍተኛ የፖለቲካ አመራር፣ በተቀናጀ የመንግሥት ሥራና በተጠያቂነት መመራት እንደሚገባው ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት በሰቆጣ ቃል ኪዳን የጀመረችውን ጉዞ በጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር፣ በተቋማዊ አሠራር፣ በየደረጃው በሚደረግ ክትትልና በተቀናጀ የበጀት ምደባ በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የመሪዎች የልምድ ልውውጥ ይህን ተሞክሮ ከማካፈል ባለፈ የሁለቱን ሀገራት አቅም በማቀናጀት ለጤናማ፣ምርታማና ብልፅግናዋን ለምታረጋግጥ አፍሪካ የጋራ መፍትሔ ለመፍጠር ዕድል እንደሚከፍትም አንስተዋል።

የሕፃናት የዛሬ ጤና የአፍሪካ የነገ ዐቅም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ እምነት የሁለቱን ሀገራት ትብብርና የመሪዎችን ቁርጠኝነት በማጠናከር፣ ለጤናማና ምርታማ ትውልድ ጠንካራ መሠረት እንጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም