ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የትኛውም አካል ሊያስቆመው አይችልም-አቶ አባዱላ ገመዳ

አዲስ አበባ፣መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የትኛውም አካል ሊያስቆመው እንደማይችል የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ባሕር በር እንድታጣ የተደረገው ምንም አይነት ውይይት ሳይደረግበት በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ አባዱላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለዘመናት ኢትዮጵያን የባሕር በር የማሳጣት ዕኩይ ሴራ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአውደ ውጊያ በተደጋጋሚ ጊዜ ባደረጉት ሙከራ ማሸነፍ እንደማይችሉ ሲረዱ የውስጥ ባንዳ ፈጥረው እንደተጠቀሙበት ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ እንደ ማሳያነት ያነሱት ከሻዕቢያ እና ሕወሃት መመስረት ጀርባ የግብጽ እጅ እንደነበረበት በመግለጽ ነው።

ታሪካዊ ጠላቶች በውስጣችን የፈጠሯቸው ኃይሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደዋዛ ተላልፎ እንዲሰጥ አድርገዋል ነው ያሉት።

በተለይም ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገው ምንም አይነት ውይይት ሳይደረግበት በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

‘’በባሕር በር ጉዳይ ላይ ያደረግናቸው፣ የተግባባንባቸው በሕጋዊ መድረክ ውይይት ተደርጎ የተወሰነ ውሳኔ የለም’’ ሲሉም ተናግረዋል።

እነዚህ ጉዳዮች ሕጋዊ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ መፈጸማቸውን አንስተው፤ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥት ሳይጸድቅ ምንም ጉዳይ ላይ መወሰን የሚያስችለው ሥልጣን የሌለው መሆኑንም አስረድተዋል።

ነገር ግን ይህንን በመጣስ ውሳኔዎቹ ውይይት ሳይደረግባቸው በጥቂት ግለሰቦች ይወሰናሉ፣ በዛው ተግባራዊ ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዚህም ሁኔታ የኢትዮጵያ ትልቁ ብሔራዊ ጥቅም የሆነውን የባሕር በር ማጣት የሚያስቆጭ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት የባሕር በር ባለቤትነቱን ጉዳይ በሰላማዊ እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ አካሄድ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የትኛውም አካል ሊያስቆመው የማይችል አይቀሬ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጥሎ ማቆየት አይቻልም” ሲሉም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም