ቀጥታ፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የሰብል ዝርያዎችን ለማላመድና ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ እና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለማላመድና ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ በርካታ ሀገር በቀል ማሻሻያዎችን በማድረግ የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

በዚህም ግብርናውን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን በዘርፉ ከፍታዋን የሚመጥኑ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የሰብል፣ የጥራጥሬ፣ የፍራፍሬና አትክልትና የእንስሳት ዝሪያዎችን በማጥናት የምርምር ውጤቶችን በማባዛት ህብረተሰቡ አውቆ እንዲጠቀም የማስቻል ተግባራትን በቀዳሚነት ያከናውናል፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት የድርሻውን በመወጣት በኩል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡ 

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬና የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የተቋሙ ቀዳሚ ተግባራት ናቸው፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ በእስካሁኑ ሂደቱ ባከናወናቸው የምርምር ስራዎች የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ 1ሺህ 700 ዝርያዎችና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙት ቡና እና መሰል ዝርያዎች እንደሚገኙበት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 


 

በምርምር በተገኙ አዳዲስ ዝርያዎች አማካኝነት የስንዴ ምርትን በሄክታር ከ15 ኩንታል ወደ 40 ኩንታል፤ በቆሎ ከ30 እስከ 40 ኩንታል ይገኝ የነበረውን አሁን ላይ በአማካይ ከ60 እስከ 70 ኩንታል ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለችው ጥረት ስኬት የላቀ ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዘርፉን ውጤታማነት በበለጠ ለማሳደግ የተቀረጸው ፖሊሲና ሌሎች ማዕቀፎችን መሰረት በማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ዝርያዎችን ማፍለቅና የማላመድ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም አግሮ- ኢኮሎጅን መሰረተ ያደረገ ዝርያ አቅርቦትና ምርት አመራረት እንዲኖር የሚያስችሉ ተግባራት  መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ መቋቋም የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ላይ በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት እየተተከሉ የሚገኙ የፍራፍሬ ችግኞች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሚተከሉ ችግኞች አፈርና ውኃን በመጠበቅ ለግብርና ግብዓትና ምርትና ምርታማነት ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም