ለመደመር መንግሥት የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶች መሳካት የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ለመደመር መንግሥት የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶች መሳካት የበኩላችንን እንወጣለን
ሚዛን አማን፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ለማከናወን ያቀዳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት አንስተዋል፡፡
በቀጣይም ለማከናወን ያቀዳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
አስር አለቃ ኃይሉ አባኑራ እንዳሉት፤ የመደመር መንግስት የልማት ትሩፋቶች ኢትዮጵያን ወደ ፊት እያራመዱ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት በተጨባጭ ማየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተሻለ ለውጥ ያስመዘግባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ በተለይ በሴራ ያጣነውን የባሕር በር መልሰን እንድናገኝ በማድረግ ተጨማሪ የልማት አቅም ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡
የመደመር መንግሥት በተለያዩ መስኮች የሚያከናውናቸው ኢኒሼቲቮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆናቸው በቀጣይም በሚከናወኑ ልማቶች ከመንግሥት ጎን እንሆናለን ብለዋል።
አቶ አለማየሁ ያኩቴት የተባሉ ሌላው ነዋሪ በበኩላቸው፤ የልማት ሥራን በማፋጠን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል ከአዲሱ መንግስት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት እስካሁን ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም አዲሱ መንግስት የልማት ስራዎችን ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳላቸውና ለእዚህም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል፡፡
መንግስት በልማት እና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ላይ ያመጣውን ለውጥ ያደነቁት ደግሞ አቶ ተዘራ ከበደ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
ሰላምን ለማጽናትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መንግስት እየተከተለ ያለውን አቅጣጫ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ የመደመር መንግስት የልማት አቅጣጫዎች ከግብ እንዲደርሱ ማገዝ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ በዚህ ረገድ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።