የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሕዝብና የኢኮኖሚ አቅም አፍሪካን በተሻለ መልኩ ለመቅረፅ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሕዝብና የኢኮኖሚ አቅም አፍሪካን በተሻለ መልኩ ለመቅረፅ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሕዝብና የኢኮኖሚ አቅም ለአፍሪካ በተሻለ መልኩ ለመቅረፅ የሚያስችል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በትብብር ሊሰሩባቸው በሚችሏቸው የሁለትዮሽ ትብብር መስኮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ትብብርና የልምድ ልውውጥ ላይ በስፋት ምክክር መደረጉን አመልክተዋል።
ናይጄሪያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን የተገኘውን ተጨባጭ ስኬት በመገንዘብ የኢትዮጵያን ልምድ ለመቅሰም በልዑካኗ በኩል ላደረገችው ጉብኝት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ በሀገራቸው የሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የሚያሳዩት ቁርጠኝነትም ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሣሠሩ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሕዝብና የኢኮኖሚ አቅም በተቀናጀ መልኩ መሠማራት አፍሪካን በተሻለ መንገድ ለመቅረጽ ያለውን ዐቅም በይበልጥ እንደሚያጎላ ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያ ለናይጄሪያ የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት አሠራሮችን ማሻሻሏን እንዲሁም የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ የናይጄሪያ ዜጎች የቪዛ ነጻ የጉዞ ሥርዓትን በሥራ ላይ ማዋሏን ገልጸዋል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሰዎች ለሰዎች ግንኙነትና የዲፕሎማሲያዊ ትሥሥር የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ዐቅም እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍም አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ እያበረከቱ ያሉትን ጉልህ አስተዋጽዖ በውይይቱ ላይ መነሳቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ሌሎች የናይጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ሊያደርጉ ስለሚችሉባቸው ዕድሎችና መወያየታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።