ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት በዲፕሎማሲው ረገድ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል

ጅማ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት በሰላም እና በዲፕሎማሲው ረገድ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጉተማ ዳንኤል፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካና ከአፍሪካ ውጭ ካሉ ወዳጅ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር የጀመረችውን የዲፕሎማሲ አካሄድ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሀገሪቱን አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ከነባር ግንኙነቶች ጋር ማጣጣም፣ ከወዳጅ ሀገራት ጋር በቀጣይነት መመካከርና በአስፈላጊ መስኮች ትብብርን ተቋማዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለዋዋጭ የዓለም ሥርዓት ውስጥ የጋራ አቅጣጫና ስትራቴጂ በመቅረጽ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በጋራ መሥራት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ያስችላታል ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ  የውስጥ አቅምን ማሳደግ፣ የውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት በበለጠ የዲፕሎማሲ አቅሟን በማጠናከር እንደ ባህር በር ያሉ ወሳኝ ብሔራዊ ፍላጎቶቿን ማስከበር እንዳለባትም መምህር ጉተማ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ፍላጎቶቿን በራሷ አቅም ለማሳካት እንደምትሠራ የገለጹት አቋም የሚደገፍ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ሰጥቶ መቀበል ያሉ የዲፕሎማሲ መርሆዎችን በመጠቀም ብሔራዊ ፍላጎቶችን ማሳካት እንደሚገባ አብራርተዋል።

ከሚቀያየረው የዓለም ሥርዓት ጋር የሚሄድ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባትም ለሀገሪቱ የወደፊት አቅም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ደሊል አሕመድ በበኩላቸው፣ የውስጥ ሰላምና አንድነት መጠናከር ሀገሪቱ የጀመረቻቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካትና ብሔራዊ ጥቅሞቿን በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ የሀገርና የሕዝብ አንድነትን ማጽናት እንደሚገባም መምህር ደሊል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም