ቀጥታ፡

የክልሉ አመራር በተደመረ አቅም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት አለበት

ሀረር ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል አመራሩ በተደመረ አቅም የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት አለበት ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በክልሉ ለተሾሙ አዳዲስ የስራ ሃላፊዎች የስራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል።


 

በመልእክታቸውም የክልሉ አመራር በተደመረ አቅም የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አጽዕኖት ሰጥተዋል።

በክልሉ ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች እመርታ የታየባቸውና ህዝብንም ተጠቃሚ ያደረጉ መሆኑን አንስተው ይህንን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ህዝቡን በማስተባበር በታማኝነት፣ በትጋትና ቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም ሌብነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የህዝብ አመኔታ ማትረፍና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አጽዕኖት ሰጥተዋል።

በተቋማት የሚስተዋሉ አንዳንድ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደሎችን በመቅረፍ በጥሩ ስነ ምግባር አገልግሎት መስጠትና አሰራርን ይበልጥ ማዘመን ይገባል ብለዋል።

በመደመር እሳቤ በመመራት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ የልማት ስራዎችን ይበልጥ ማስፋትና ለስኬት ማብቃት እንደሚገባም ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም