ቀጥታ፡

የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ተገቢውን ምላሽ ይሻል

አዶላ/ነገሌ ቦረና፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ተገቢውን ምላሽ እስከሚያገኝ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ የደቡብ ኦሮሚያ  ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። 

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች፤ መንግሥት የህልውና ጉዳይ የሆነውን የባህር በር በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።

የባህር በር የማግኘቱ ጥያቄ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለደህንነት ወሳኝ በመሆኑ ተገቢውን ምላሽ ይሻል፤ እኛም ጥያቄው ወደ ተግባር እስኪቀየር ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉም ነው ነዋሪዎቹ የገለፁት።

ከነዋሪዎቹ መካከል የአዶላ ከተማ ነዋሪው አቶ አሸናፊ ደንቆ በከተማዋ የተጀመረውን ልማት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።


 

መንግሥት የባህር በርን በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ "የባህር በር የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ እንጂ የቅንጦት ጥያቄ እንዳልሆነ ዜጎች ሁሉ እንረዳለን" ብለዋል።

ጉዳዩ ታሪካዊና ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንና ሁሉም ከተባበረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እንደሚመጣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ልምድ ምስክር መሆኑን አስታውሰዋል።

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ እሸቱ ኃይሉ በበኩላቸው፤ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

መንግስት እያደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ተግባር እስኪቀየር ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ረሂማ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ መንግሥት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የባህር በር ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም