በከተማው የመሬት ካዳስተር አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታላይዝ በመደረጉ ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የመሬት ካዳስተር አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታላይዝ በመደረጉ ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት አስችሎናል
ጅማ ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ በጅማ ከተማ በመሬት ጽሕፈት ቤት የሚሰጡ የካዳስተር አገልግሎቶች መዘመናቸው ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።
ከዚህ ቀደም በጽሕፈት ቤቱ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ጊዜ ከመጠበቅ ባለፈ መረጃ ለማግኘት ብቻ ከአሥር ቀናት በላይ ይመላለሱ እንደነበር ተገልጋዮቹ አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት የመረጃ አያያዙ መደራጀቱና አገልግሎቱ ዲጂታል መሆኑ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ መሐመድሳሊ ማሞ ለካዳስተር አገልግሎት ወደ ጽሕፈት ቤቱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ጊዜና ገንዘባቸው ሳይባክን ባጠረ ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ ካርታ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም መረጃቸው መለያ ቁጥር ተሰጥቶት በኮምፒዩተር በተደራጀ መልኩ መመዝገቡ አገልግሎቱን ለመከታተል እንዳመቻቸው ተናግረዋል።
ሌላው ተገልጋይ አቶ አሚን አባሞጋ ባለጉዳዮች የሚጠበቅባቸውን ሙሉ መረጃ ይዘው ከቀረቡ አገልግሎቱን በፍጥነት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
አቶ አሚን እንደሚሉት፣ የሚጠበቅባቸውን መረጃ አሟልተው በመቅረባቸው ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት አግኝተዋል።
አቶ በደዊ ጀማል በበኩላቸው፤ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም በጠባብ ሕንፃ ውስጥ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው፣ የመብራት መቆራረጥ አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ መረጃዎች ጠፍተው ለወራት ሲፈለጉ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ያለ ወረቀት ንክኪ በተሰጣቸው መለያ ቁጥር ፋይላቸውን አስወጥተው የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የጽሕፈት ቤቱ የካዳስተር መሬት ምዝገባ የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ገዛሊ ከድር፣ መንግሥት የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግና የዜጎችን ጥያቄ ለመመለስ ባስቀመጠው አቅጣጫ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ዲጂታል ካርታ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ የካዳስተር አገልግሎቱ በከተማዋ ከሚገኙ 13 ቀበሌዎች በ12ቱ መጠናቀቁን አብራርተዋል።
በዚህም እስካሁን ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች በዘመናዊ ካዳስተር ተመዝግበው ካርታ ወስደዋል ብለዋል፤ ቀሪዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።
የጅማ ከተማ መሬት ካዳስተር አገልግሎት ዲጂታል መሆኑ የመረጃ አያያዝን ከማዘመን ባለፈ፣ ተገልጋዮች ጊዜና ወጪያቸውን ቆጥበው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑ ተጠቁሟል።