የመደመር መንግስት ለኢትዮጵያ እድገት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ የትውልዱ አደራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ለኢትዮጵያ እድገት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ የትውልዱ አደራ ነው
ሀረር ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ለኢትዮጵያ እድገትና ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ በኩል ትውልዱ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የትምህርት ባለሞያዎች ገለጹ።
የመደመር መንግስት በይፋ ተመስርቶ በቀጣይ መንግስት የሚያከናውናቸውን አበይት ተግባራት በተመለከተ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገራዊ ትልሞችን አልፎም ቀጣናዊና አህጉራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያመላከተ ሰፊ ንግግር አድርገዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ባለሞያዎች፤ ርዕሰ ብሄሩ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሃሳቦች ተግባራዊ ከተደረጉ ሀገርንና ትውልድን ወደ ፊት የሚያራምዱ ናቸው ብለዋል።
የስነ ዜጋና የስነ ምግባር መምህር የሆኑት ቶማስ ዱባለ፤ የመደመር መንግስት የሀገርን እድገት፣ ልእልና እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደም እየሰራ ውጤትም እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ የተመሰረተው መንግስትም መልካም ጅምሮችን በማስቀጠል፣ ልማትና እድገትን በማፋጠን ለሀገር ልእልና መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ተደርገው ስራቸው የተጀመረውን የጉባ ብስራቶች ለስኬት ማብቃት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ለማሳካት ትውልዱ እያነሳ ያለውን ጥያዌ ሀገር እየመራ ያለው መንግስት ለማሳካት መትጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሌሎች የትምህርት ባለሞያዎች ምስራቅ ጥላዬ እና ወንደሰን ግርማ፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለሀገር ልማት እድገትና ማንሰራራት ከመንግስት ጎን ቆመን እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በትውልድ ግንባታና ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት የመንግስት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያዊያን ለጋራ ዓላማ ተደምረን ለሁሉም የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት ለኢትዮጵያ እድገትና ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ የትውልዱ አደራ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።