ቀጥታ፡

የኢፌዴሪ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ልዩ ስብሰባው በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ እየተወያየ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2019(ኢዜአ)፦ 7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ልዩ ስብሰባው፣ በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ እየመከረ ይገኛል።

የምክር ቤት አባል እና የመንግሥት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሠማ በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል።


 

በቀረበው ማብራሪያም፣ ከዚህ በፊት በነበሩት 22 አስፈጻሚ አካላት ላይ የቁጥር ልዩነት እንደሌለ እና ከቁጥር አንፃር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በነበሩበት 22 ሆነው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

ይህም ሆኖ በሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ብቻ የስያሜ ለውጥ መደረጉን እና ሁለት ሚኒስቴሮች እንደ አዲስ መቋቋማቸው ተብራርቷል።

እንደ አዲስ የተቋቋሙት ሁለት ሚኒስቴር መ/ቤቶች ቀድሞ "የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር" የነበረው በአዲሱ "የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር" በሚል እና ቀድሞ "የቱሪዝም ሚኒስቴር" የነበረው በአዲሱ "የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር" በሚል መቋቋማቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ቀድሞ "የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር" የነበረው "የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር" በሚል እና ቀድሞ "የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር" የነበረው "የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር" በሚል ስያሜያቸው መቀየሩ ተገልጿል።


 

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ላይ ማሻሻያው ያስፈለገበት ምክንያት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ከተልዕኳቸው ጋር ለማጣጣም መሆኑም ተብራርቷል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እያቀረቡ እንደሚገኙ የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

እንደ አዲስ በተቋቋሙት ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ሆነ የስያሜ ለውጥ በተደረገባቸው ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ዙሪያ በቀጣይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም