የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ ትውልድ እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ ትውልድ እየተገነባ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፡ አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በሥነ-ምግባርና በሀገር ፍቅር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት በአጽንኦት አሳስበዋል።
ይህ ጥሪ የትውልድ ግንባታን የሀገሪቱ የወደፊት አቅም፣ ህልውና እና ሉዑላዊነት መሠረት አድርጎ የሚያስቀምጥ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ነው።
ይህ መልዕክት የነገ ተስፋን በቃልና በምኞት ብቻ ማቅረብ ሳይሆን፣ ዛሬ በፅኑ መሠረት ላይ የሚገነባው የሰው ኃይል ነገ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስና ፖለቲካዊ አቅም ሙሉ በሙሉ የሚወስን መሆኑን የሚያመላክት እይታ ነው።
የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው በዚህ ታሪካዊ ጉዞ፣ ወጣቶች የለውጥ ተከታዮችና ተመልካቾች ብቻ ሳይሆኑ የፊተኛው መስመር መሪዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች እና ዋና ውሳኔ ሰጪዎች መሆን አለባቸው።
በዛሬው ፈጣን፣ ውስብስብና ተለዋዋጭ ዓለም ወጣቶች ወደ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አመራር ግንባር ቀደምትነት መምጣት የሚገባቸው በዋናነት በሚከተሉት ቁልፍ ምክንያቶችና ምሰሶዎች ምክንያት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓለም የምትመራውና የኃይል ሚዛኗ የሚወሰነው በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ የበላይነት ፉክክር ነው። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ የሳይበር ደህንነት (Cybersecurity)፣ የዳታ ሳይንስ (Data Science) እና ዲጂታል ኢኮኖሚ የዓለምን የፖለቲካና የሀብት አሰላለፍ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ።
ስለሆነም የነገው የኢትዮጵያ ትውልድ በነዚህ ዘመናዊ የዕውቀት መስኮች ማለትም በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ፣ በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂና ምግብ ዋስትና፣ በጤና ጥበቃና ህክምና ሳይንስ፣ በኢንዱስትሪ፣ በግንባታና በማኑፋክቸሪንግ፣ በታዳሽ ኃይልና ማሽነሪ፣ በዲጂታል አገልግሎትና ሶፍትዌር ልማት፣ እና በሌሎች በርካታ ስትራቴጂካዊ ሙያዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የመምጠቅና የማደግ ግዴታ አለበት።
ወጣቱ ትውልድ የዲጂታል ዘመን ተወላጅ (Digital Native) በመሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመረዳት፣ የመተግበርና ወደ አዲስ የፈጠራ ውጤት የመቀየር ተፈጥሮአዊ ዝንባሌና ዝግጁነት አለው።
በዛሬው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መቆም የሚቻለው በባህላዊና ያረጁ አሰራሮች ሳይሆን በየዕለቱ ተሻሽሎ፣ ጠንክሮና በርትቶ በመገኘት ብቻ ነው። ወጣቶች በሀገሪቱ የውሳኔ ሰጪነትና የመሪነት ቦታ ላይ ሲቀመጡ የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን (Digital Transformation) በከፍተኛ ፍጥነት ማፋጠን ይችላሉ።
ይህንን እውን ለማድረግም ወጣቶችን በፕሮግራሚንግና በዲጂታል ክህሎት ለማብቃት የተጀመረው የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደሮች (5 Million Coders) ፕሮጀክት፣ የሀገሪቱን የሰው ኃይል አቅም ከአዲሱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ለማጣጣም የተቀመጠውን ግልጽ አቅጣጫ ያሳያል።
በተጨማሪም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተኮር ተቋማት በሰፊው እየተገነቡና እየተስፋፉ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና ተካፋይነት አልፋ ወደ ቴክኖሎጂ ፈጣሪነትና ምንጭነት ለመሸጋገር ያላትን ጽኑ ፍላጎት ያመላክታል።
በአሁኑ ወቅት የዓለም ፖለቲካ ሁኔታ በየዕለቱ የሚቀያየር፣ ያልተረጋገጠ እና እጅግ ውስብስብ መስመር የሚይዝ ነው። በዚህ ዘመን የሀገር ሉዓላዊነት እና የህዝብ ክብር የሚጠበቀው በወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ በዲጂታል ደህንነት እና በፖለቲካዊ/ዲፕሎማሲያዊ ብልህነት ነው።
ዓለም ወዴት እየሄደች እንደሆነ በቅርበት የሚከታተል፣ መረጃዎችንና ሁነቶችን በጥራት በመተንተን ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስከብር፣ እንዲሁም ፈጣንና ስትራቴጂካዊ ውሳኔ መስጠት የሚችል የወጣት መሪዎች ስብስብ ካልኖረ ሀገር ለውጫዊ ተፅዕኖ፣ ጫና እና ጥቃቶች ተጋላጭ ትሆናለች።
ስለሆነም ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ የኢኮኖሚ ነፃነቷ የተረጋገጠ እና የማትደፈር ኢትዮጵያን ለማቆም የዓለምን የኃይል አሰላለፍ በሚገባ መረዳትና መምራት የሚችሉ ብስል ወጣት መሪዎች ወሳኝ ናቸው።
ኢትዮጵያ በፅኑ የምትፈልገው በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርተው የሚከራከሩ፣ ልዩነቶችን በሰለጠነ ውይይት የሚያቀርቡ፣ የሌላውን ሀሳብ በትዕግስት የሚያዳምጡና ለጋራ ጥቅም የሚቆሙ ወጣቶችን ነው።
ወጣቶች ወደ አመራር መድረክ ሲመጡ አዳዲስና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ባህሎችን በማስተዋወቅ ሀገሪቱን ከኋላቀር የፖለቲካ አዙሪት ወደ ልማት፣ ዕድገትና ህብረት መምራት ይችላሉ። አንድ ሀገር ጠንካራና ዘላቂ መሠረት የሚኖራት የትውልድ ሽግግሩ በሥርዓት፣ በሰላም፣ በስልጠናና በበቂ ዝግጅት ሲካሄድ ብቻ ነው። ወጣቶች ዛሬውኑ በውሳኔ ሰጪ ቦታዎች ላይ መሳተፍ ካልጀመሩና ተግባራዊ ልምድ ካላካበቱ፣ የነገዋን ሀገር የመረከብና የመምራት ብቃታቸው አጠራጣሪ ይሆናል።
ወጣቶች የቴክኖሎጂና የሳይንስ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅር፣ የኃላፊነት ስሜት፣ ታማኝነትና የላቀ ሥነ-ምግባር ያላቸው መሪዎች ሆነው ሲወጡ ሀገርን ከማንኛውም ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች በፅናት መከላከል ይችላሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ "አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ አዲሱ ትውልድ መዘጋጀት አለበት" የሚለው ጥሪና መልዕክት፣ ትውልዱን ለነገ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ለዛሬው የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥም ንቁና ግንባር ቀደም ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ያሳስባል።
የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋና ህልውና ያለው በወጣቶቿ እጅ ውስጥ ነው፤ ይህንን ተስፋ ደግሞ ወደ ተጨባጭ እውነታ የመቀየር ሀገራዊ ኃላፊነት የሚጀምረው ከዛሬው የትውልድ ግንባታ ሥራ ነው።