ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

ጨዋታው ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም  ይካሄዳል።

ብሔራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ2028  በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው 34ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ ማጣሪያ ከሩዋንዳ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ከመስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅቱን አድርጓል።

በለሜቻ ግርማ የሚሰለጥነው ቡድን ከሲሸልስ አቻው ጋር ሁለት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች አከናውኗል።

በዚህም ሉሲዎቹ 16 ለ 0  እና 10 ለ 0 አሸንፈዋል።  በነዚህ ጨዋታዎች 26 ጎሎቹን በማስቆጠር ቡድኑ ፍጹም የበላይነቱን ይዟል።

ቻለው ለሜቻ በሁለት ዓመት ውል የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት ነው።

በአንድሬ ካሳ ሙቡንጎ የሚመራው የሩዋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላለፉት 10 ቀናት ዝግጅቱን በኪጋሊ ሲያደርግ ቆይቷል።

ሙቡንጎ በመጀመሪያ ዙር ለ29 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው በሂደት አራት ተጫዋቾችን ቀንሰው ለጨዋታው ተዘጋጅተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የመልስ ጨዋታቸውን ጥቅምት 3 2019 ዓ.ም በአበበ በቂላ ስታዲየም ያከናውናሉ።

በደርሶ መልስ ውጤት ሉሲዎቹ ካሸነፉ ሶስተኛውን ዙር ይቀላቀላሉ።

ብሔራዊ ቡድኑ በፊፋ የሴቶች የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ እና ከዚህ ቀደም በነበሩ ማጣሪያዎች በነበረው የተሻለ ብቃት የቅድመ ማጣሪያ ሳያደርግ ወደ ሁለተኛ ዙር ቀጥታ ገብቷል።

በአምስት ዙሮች በሚካሄደው ማጣሪያ ሁለት ሀገራት አፍሪካን ወክለው በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።

በአጠቃላይ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ 12 ሀገራት የሚሳተፉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዚኛውን ሳይጨምር ከዚህ ቀደም በአራት የኦሊምፒክ ማጣሪያዎች ላይ ተሳትፈዋል።

እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ ባደረገው የማጣሪያ ተሳትፎ መጨረሻ ዙር የደረሰበት ትልቁ ውጤቱ ነው።

በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ በድምር ውጤት 3 ለ 1 ተሸንፎ ለኦሊምፒኩ ማለፍ አልቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም