የመደመር እሳቤ-ለግዙፍ ሀገራዊ ውጥኖች ስኬት - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ-ለግዙፍ ሀገራዊ ውጥኖች ስኬት
የመደመር መንግሥት እና እሳቤ የተበታተነ አቅምን በማሰባሰብ፣ሀገር በቀል እውቀቶችን መሠረት በማድረግ እና የሕዝብ ተሳትፎን በማስተባበር ግዙፍና ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ ውጥኖችን ማሳካት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ፍልስፍና ነው።
ይህ እሳቤ ወረቀት ላይ ብቻ የቀረ ሳይሆን፣ ውስን ሀገራዊ ሃብትን በአንድ ላይ በማቀናጀት አዳዲስ የሥራ ባህሎችንና ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣት የቻለ እሳቤ መሆኑን በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ያረጋግጣሉ።
የመደመር እሳቤ ዋና ግብ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት ተግባራት የሀገሪቱን የልማት ምዕራፍ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል።
በኢኮኖሚ እና በመሠረተ-ልማት ዘርፎች የታዩት ተጨባጭ ማሳያዎች የመደመር እሳቤ ያለውን ትልቅ የማስፈጸም አቅም በግልጽ ያሳያሉ።በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ኢትዮጵያን የአፍሪካ ትልቁ የስንዴ አምራች ያደረገው የስንዴ ልማት እመርታ እና በሕዝብና መንግሥት ትብብር ግንባታው የተከናወነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚሁ እሳቤ ፍሬዎች ናቸው።
በተጨማሪም ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የከተሞችን ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት እንዲሁም በአጭር ጊዜ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎችን የገነቡት የ“ገበታ ለሸገር”፣ “ገበታ ለሀገር” እና “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች የመደመር ስልታዊ አካሄድ ግዙፍ ውጥኖችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚችል ማረጋገጫዎች ናቸው።በመደመር መንግሥት ምስረታ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ይህንን እሳቤ ይበልጥ የሚያጠናክሩ ቁልፍ ሐሳቦችን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንጩን የሚረሳ ወንዝ እንደሚደርቅ ሁሉ፣ መሠረቱንና ሀገራዊ እሳቤውን በመጣል የሚጀመር የሥልጣኔ ጉዞ ሩቅ ሊጓዝ እንደማይችል ገልጸው፤ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያዊነት መሠረት የሆነውን የመደመር እሳቤን በተሟላ ሁኔታ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል።
አዲሱ የመደመር መንግሥት የሀገር ውስጥ እሴቶችን ከውጭው ጠቃሚና ተራማጅ ዕውቀት ጋር በማዋሃድ አዲስ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ለመገንባት እንደሚሠራ አስምረውበታል።
በተጨማሪም በትናንቱ ንግግራቸው የመደመር ፖለቲካዊ ባህሪ ልዩነቶችን አቀናጅቶ የጋራ ውጤት መፍጠር መሆኑን በመጥቀስ፣በምርጫ ውድድር ውስጥ የፓርቲዎች ማሸነፍና መሸነፍ ቢኖርም እንኳ ውጤቱ ሲደመር ኢትዮጵያ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ልጆች የሌሏት ሀገር መሆኗን ማሳየት ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ከተናጠል ዘርፍ ወደ ብዙሃ ዘርፍ በመሸጋገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በኮሪደርና ቱሪዝም ልማት የተመዘገቡት አስደናቂ ውጤቶች ሁሉ የተናጠል አቅሞችን በማቀናጀት (Synergy) የመጡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት አዳዲስ ዕድሎችን ወደ ውጤት በመቀየር እና የጀመራቸውን ግዙፍ ስራዎች በተከታታይነት በማስቀጠል ታላቅ ሀገር የመገንባት ርዕዩን አፅንቶ የሚቀጥል ነው።